የትግራይ የዘር ማጥፋት አጣሪ ኮሚሽን፣ በጦርነቱ በአምራቹ ዘርፍ እና በሕዝቡ የገቢ ምንጮች ላይ ከ83 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት እና ኪሳራ መድረሱን ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። ከአጠቃላዩ የገንዘብ ጉዳት እና ኪሳራ 26 በመቶ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ መድረሱን የጠቀሠው ሪፖርቱ ይህም በገንዘብ ሲተመን 21 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቅሷል። በንግድ ላይ የደረሰው ጉዳትና ኪሳራ 20 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳትና ኪሳራ 19 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ሪፖርቱ አመልክቷል። በአምራቹ ዘርፍ ላይ የደረሰው “ቀጥተኛ ጉዳት” ብቻ 33 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም ተገልጧል።