የኬንያ የጸረ ሽብር ፖሊስ፣ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያው አማጺ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ነው ያለው ሳዳም ቡኬ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ መናገሩን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ሳዳም ቡኬ፣ በሰሜናዊ ኬንያ በመርሳቢት እና ኢሲዮሎ አውራጃዎች የቡድኑ መሪ እንደኾነ ፖሊስ መግለጡን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።
የቡድኑ መሪ በቁጥጥር ሥር የዋለው፣ የአገሪቱ ጸጥታ ኃይሎች በኹለቱ አውራጃዎች የወንጀል መረብ በመዘርጋት በአገሪቱ ብሄራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ ደቅኗል ባሉት በቡድኑ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።
የኬንያ የጸረ ሽብር ፖሊስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኹለቱ አውራጃዎች የሱማሊያውን አልሸባብን በሽብር ድርጊቶች በመርዳት፣ የአደንዛዥ እጽ፣ የሰዎችና ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በማካሄድ፣ የማስለቀቂያ ገንዘብ ማካበትን ዒላማ ያደረገ የሰዎች እገታ በመፈጸም፣ ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮ በማካሄድ እና የጎሳ ግጭቶችን በመቀስቀስ ወንጀሎች ተሠማርቷል በማለት ይከሳል።