ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ “ማንነት” እና ኃይማኖት-ተኮር” ጥቃቶች መንግሥታዊ መዋቅሮችን የተከተሉ ስለመኾናቸው ምርመራ ያድርግ

መኢአድን፣ እናት ፓርቲንና ኢሕአፓን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች የመሠረቱት ጥምረት፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ “ማንነት” እና ኃይማኖት-ተኮር” ጥቃቶች መንግሥታዊ መዋቅሮችን የተከተሉ ስለመኾናቸው ምርመራ እንዲያደርግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን ያወገዘው ጥምረቱ፣ የኃይማኖት አባቶች የጅምላ ግድያዎች እንዲቆሙ በመንግሥትና ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቋል። ጥምረቱ፣ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኾነው ይሠራሉ ላላቸው ባለሥልጣናት፣ ጥቃቶችን “በቸልታ” ያልፋሉ ላላቸው የጸጥታ አካላት እንዲኹም ጥቃቶችን አይዘግቡም ላላቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ወደፊት ከተጠያቂነት አታመልጡም የሚል መልዕክት በዚኹ መግለጫው ላይ አስተላልፏል።