ኤርትራ ለኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት ተጠያቂ እንዳልኾነች ኹሉ የኢትዮጵያን የባሕር በር ሕልም እውን የማድረግ ግዴታም የለባትም

ኤርትራ፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ለመግታት የመከላከያ ኃይሏን በማጠናከርና ቀጠናዊ ተጽዕኖዎችን በመፍጠር ላይ መኾኗን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚንስቴር ዛሬ ለኤርትራ ሕዝብ በትግሬኛ ባሠራጨው ጽሁፍ ላይ አስታውቋል። ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራትና ዓለማቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያን አካሄድ እንዲያወግዙና ኢትዮጵያ ቀጠናዊ ግጭት ከመቀስቀስ እንድትቆጠብ ግፊት እንዲያደርጉ የጠየቀው ሚንስቴሩ፣ ኤርትራ ከቀይ ባሕር አዋሳኝ አገራት ጋር የኹለትዮሽ ትብብሯን ለማጠናከር ጥረት እያደረገች መኾኗን ገልጧል። ሚንስቴሩ፣ ኤርትራ ለኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት ተጠያቂ እንዳልኾነች ኹሉ የኢትዮጵያን የባሕር በር ሕልም እውን የማድረግ ግዴታም የለባትም ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ “የጅዖፖለቲካ በደል” እንደተፈጸመባትና የችግሮቿ ምንጭ “የባሕር በር አልባነት” እንደኾነ በመስበክ፣ ሕዝቡ “በቁጭት እንዲነሳሳ” በመቀስቀስ ላይ ነው በማለትም ሚንስቴሩ ወቅሷል።