አብይ አሕመድ ለትግራይ ብሎ የጻፈው ደብዳቤ የአሸባሪነት መንፈስ ያዘለ በትግራይ ህዝብ ላይ እየቀጠለ ያለው በደል አካል ነው

🔴 ”  በትግራይ በማንኛውም መመዘኛ ጦርነት የሚጋብዝ አንዳች ሁኔታ የለም ” – በሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት

🚨” በአሁኑ ወቅት በትግራይ በማንኛውም ደቂቃ በሆነ ሰው በሚፈጠር ስህተት ለግጭት የሚዳርግ ሁኔታ ሰፍቷል ” – አቶ ጌታቸው ረዳ

ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ተንተርሶ ለትግራይ ህዝብ በተለይም ለትግራይ ሊህቃን ጠንካራ መልዕክት እና ምክር ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው ፥ ” ህዝቡ ያለፈው አልበቃ ብሎት የትናንት ቁስሉ ሳይሽር አሁንም በሽብር እና በጦርነት ወሬ ስሜት ወስጥ ይገኛል ” ብለዋል።

በፓለቲካ ፣ በንግድ ፣ ፀጥታ ፣ አካዳሚ እና ሚድያ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ የትግራይ ልሂቃን ወገኖች ባስተላለፉት መልዕክት ” የትግራይ ህዝብ እስከ ዛሬ የተሰቃየው የከፈለው ዋጋ ይብቃው ፤ ልዩነትን በመነጋገር እና በውይይት የመፍታት ባህልንና ልምድ ታጠቁ ” ብለዋል።

ልሂቃኑ ከፌደራል መንግስት እና ሌሎች ሃይሎች ያላቸው ልዩነት በአገሪቱ ህገ-መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግባባት ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚመራው ህወሓት የፓለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ሄር ምላሽ ያሉትን ሰጥተዋል።

ምላሹን የሰጡት 50ኛው ዓመት የትግራይ ህዝብ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።

በደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት የፓለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት  ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ሄር ምን አሉ ?

➡️ ” ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ህልውና የነበረው ተሳትፎ አስመልክተው የተጠቀሙበት አገላለፅ ልክ ነው። የትግራይ ህዝብ ሚና ባሉት ደረጃ ነው መገለፅ ያለበት ብለን እናምናለን። የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ነፃነት ፣ ልማት እና ዴሞክራሲ የከፈለው ዋጋ እጅግ ውድ ነው። እሳቸው በፅሁፋዊ መልእክታቸው የተጠቀሙበት አገላለፅ የምንጋራው እና ክብር የምንሰጠው ነው ” ብለዋል።

➡️ ” የመልእክታቸው አንኳር ነጥብ ህዝቡ ጦርነት ስለማያስፈልገው የትግራይ መሪዎች እና ልሂቃን ልብ ግዙ ተመካከሩ የሚል ነው።  የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ህዝብ ጦርነት አይወድም ፤ አይገባውም። በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብም ጦርነት አያስፈልገውም። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ ባለፉት 100 ዓመታት ከማእከላዊ መንግስቱ ያደረጋቸው ጦርነቶች ከመሬት ተነስቶ ያደረጋቸው ተንኳሽ እንደሆነ በሚያደምጥ መልኩ በደብዳቤው የቀረበ አገላለፅ ልክ ነው ብለን አንወስድም ” ሲሉ ተናግረዋል።

➡️ ” የትግራይ ህዝብ ላለፉት 100 ዓመታት እና ከዛ በላይ የተዋጋው የሚወሩትን ፣ መብቱን የሚነፍጉትን እና ድምፁን የሚያፍኑትን ለመከላከል ሲባል መሆኑ ልብ ማለት ይገባል።  ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ጦረኛ እና ተንኳሽ በሚመስል መልኩ  የቀረበ አገላለፅ ልክ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ትናንት ፣ ዛሬ ይሁን ነገ አይገዛም አይምበረከክም። ልግዛህ ላምበረክክህ ለሚለው ወራሪ መልሱ እምቢ ነው። ከዚህ ውጭ  ጦርነት ጀማሪ ሆኖ አያውቅም ፤ ማንንም ሄዶ አይወርም ልግዛህ አይልም  ፤ ስለሆነም ጦርነት ጀማሪ በሚመስል የቀረበው አገላለፅ ልክ አይደለም ” ብለዋል።

➡️ ” እኛ እንወረራለን እንጂ አንወርም ፤ ጦርነት ይከፈትብናል እንጂ በማንኛውም ህዝብ ላይ ጦርነት አንከፍትም ” ሲሉ ገልጸዋል።

➡️ ” ማንኛውም የትግራይ ፓለቲካዊ ፓርቲ ፣ ስቪክ ማህበር እና ህዝቡ ከማንኛውም ህዝብ በላይ በጦርነት የወደመ የተጠቃ ፣  ጦርነት እጅግ አፍራሽ መሆኑ ስለሚያውቅ አሁንም የጦርነት ፍላጎት የለውም ” ብለዋል።

➡️ ” በትግራይ በኩል ለጦርነት የሚጋብዝ አንድም ምክንያት የለም ። እርግጥ ነው በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ልዩነት እና መሳሳብ አለ።  ይህንንም በሰለጠነ የፓለቲካ አግባብ ይፈታ እንደሆነ እንጂ ወደ ጦርነት የሚመራ ምክንያት ሊሆን አይችልም ” ሲሉ ተናግረዋል።

➡️ ” ያለንን የፓለቲካ ልዩነት በውይይት እና በሰለጠነ የፓለቲካ አግባብ እንፈታዋለን እንጂ ወደ ጦርነት የሚያስገባን አይሆንም ” ብለዋል።

➡️ ” ከፌደራል መንግስት ጋር የሚያገናኘን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ነው። ስምምነቱ ማእከል በማድረግ የጎደለን ነገር በውይይት ለሞምላት ነው ‘እንወያይ ‘ የሚል ጥሪ እያቀረብን ያለነው። እንወያይ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈፃሚ ይሁን ፣ ወራሪዎች በሃይል ከያዙት ግዛታችን ይውጡ ፣ የግዛት አንደነታችን ይከበር ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ይመለሱ ፣ የሁለትዮሽ ፓለቲካዊ ውይይት ይጀመር ወደ መደበኛው ህገ-መንግስታዊ  ስርዓት የምንመለስበት ሁኔታ ይፍጠን ብሎ መጠየቅ የጦርነት መንስኤ ሊሆን አይችልም ” ብለዋል።

➡️ ” የ2013 ዓ.ም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ሳምታት ቀደም ብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ የአሁኑ አይነት ተመሳሳይ የፅሁፍ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር። ያኔም ‘ ወደ ትግራይ ማሰክ እንጂ የጥይት ቁምቡላ አንልክም ‘ ተብሎ ነበር። ቅኔ ነው የነበረው። አሁንም በውጭ ሲታይ ለስላሳ እና ጣፋጭ ውስጡ ሲታይ ግን ‘ ተጠንቀቁ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ሁኔታ ነው ያለው ‘ የሚል እንድምታ ያለው ደብዳቤ ነው የተሰራጨው ” ብለዋል።

➡️ ” ደብዳቤው ሆን ተብሎ ህዝብ ለማሸበር የተደረገ ነው። ይህ በትግራይ ህዝብ ላይ እየቀጠለ ያለውን በደል አካል አድርገን ነው የምንቆጥረው። የትግራይ ህዝብ ማስፈራራት አይገባም። አሁንም ‘ መጣሁብህ ገደልኩህ ‘ ማለት ለትግራይ ህዝብ ተገቢ አይደለም። የትግራይ ህዝብ አሁን የሚያስፈልገው የበደል ካሳ ፣ ሰላም ፣ ልማት እና ውይይት ነው  በመሪዎች መካከል የተፈጠረው የፓለቲካ ልዩነት በሰለጠነ ውይይት መፍታት ያስፈልጋል ” ብለዋል።

➡️ ” በአሁኑ ወቅት ህወሓትም ሆነ የትግራይ ህዝብ የጦርነት ፍላጎት የላቸውም። በመላው ትግራይ ጦርነት የሚጋብዝ እንዳች ምልክት የለም። መብታችን ፣ ማንነታችን ይከበርልን ፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ሁሉም ነገር ይፈፀም የሚል ግን ጥያቄያችን አስኪመለስ ድረስ የምናቆመው አይደለም  ይህ ዓይነት ጥያቄ በፍፁም የጦርነት መንስኤ ሊሆን አይችልም ” ብለዋል።

➡️ ” በትግራይ ለጦርነት የሚጋብዝን አንዳች ነገር የለም ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት 50ኛው ዓመት የትግራይ ህዝብ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 በጊዚያዊ አስተዳደሩ ለማክበር እየተደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት የክልሉ ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

አቶ ጌታቸው በዚሁ ወቅት በህወሓት አመራሮች መካከላል ባለው ክፍፍል የግጭት ስጋት ስለመኖሩ ጠቋሚ ቃል ሰጥተዋል።

” በአሁኑ ወቅት በትግራይ በማንኛውም ደቂቃ በሆነ ሰው በሚፈጠር ስህተት ለግጭት የሚዳርግ ሁኔታ ሰፍቷል ” በማለት ነው ስጋታቸው የገለጹት።

ትግራይ ክልል ከአስከፊው ጦርነት ገና በቅጡ ያላገገመ ሲሆን አሁን ደግሞ ህዝብን በከፍተኛ ስጋት ላይ በጣለ የአመራሮች ክፍፍል እየታመሰ ነው።