ኢዜማ፣ ብልጽግና ፓርቲ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመንግሥት ሠራተኞችን የራሱ አባላት ለማድረግ የተለያዩ “ጫናዎች” እያሣደረ ይገኛል በማለት ከሷል። ኢዜማ፣ ገዢው ፓርቲ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ለራሱ መጠቀሚያ ማድረጉን ባስቸኳይ እንዲያቆምም ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ኢዜማ፣ የገዥውን ፓርቲ ድርጊት የመገናኛ ብዙኃን እንዲያጋልጡ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲያወግዙትና ዜጎች በጋራ እንዲቃወሙት ጥሪ አድርጓል። ይህ ካልሆነ ግን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ “የሕልም እንጀራ” ኾኖ ይቀራል በማለት ኢዜማ አስጠንቅቋል።