የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል፣ የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ በባሕር በር ጉዳይ ላይ የሚከተለው “አምታች የኾነ አካሄድ” በቀጠናው ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል። የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በኤርትራ ላይ “የጦርነት ዛቻ” ማሰማት ቀጥለዋል በማለት የከሠሡት የማነ፣ በሌላ በኩል ደሞ ብልጽግና ኢትዮጵያን ከምጽዋ፣ አሰብ እና ከጅቡቲዋ ታጁራ ወደብ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሐዲድ ለመገንባት እንዳቀደ በመግለጽ “አምታች አካሄድ” ይከተላል በማለት ተችተዋል። ይሄ የፓርቲው እሳቤ ግን “ከቅን ልቦና ከመነጨ ፍላጎት” እና “ከቀጠናዊ የሰላምና ትብብር ፖሊሲ” ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም ሲሉ የማነ አጣጥለውታል።