ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት የዶ/ር አንዱአለም ዳኘን ህልፈትን ተከትሎ ምን ውሳኔ አሳለፈ ?
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ከዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አመራር አካላት ጋር የዶ/ር አንዱአለም ዳኘን ህልፈት ተከትሎ መሰራት ባለባቸው ስራዎች ዙሪያ ውይይት ማካሄዱን ገልጿል።

ውይይቱ በተለይ ቤተሰቦቹ ሊደገፉ በሚችሉባቸውና ሃኪሙ በህይዎት ዘመኑ ያከናወናቸው ልዩ ሙያዊ አስተዋጽኦችን መዘከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ዶ/ር አንዱአለም ምንም እንኳን የተሰጠውን ጸጋ ሳይሰስት በመጠቀም ለበርካቶች የዘርፉ ባለሙያዎችና በሙያው ላገለገላቸው በርካታ ህሙማን የቅን አገልጋይነት ተምሳሌት የነበረ እንቁ ባለሙያ ቢሆንም ገና በ37 ዓመቱ የተቀጠፈ በመሆኑ ለህጻናት ልጆቹና ቤተሰቡ ትቶ ያለፈው ቤትም ሆነ ሌላ ንብረት የሌለው መሆኑ ተገልጿል።

የቀረቡለትን በርካታ ዓለምአቀፍ የስራ ቅጥር ግብዣዎች ባለመቀበል ወገኑን ለማገልገል ቆርጦ የነበረ ባለሙያ ከመሆኑም በላይ በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀዶ ጥገና ክፍል የነበረውን ልዩ አበርክቶና የቀዶ ጥገና ክፍሉን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሻሻል እየጣረ የነበረ እና እውን ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሶ ያለፈ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የነበረውን ሞያዊ አቅም ተጠቅሞ ራሱን ለተገልጋዮች በቅንነት ሰጥቶ ያለፈ ታላቅ ባለሙያ እንደነበረ የስራ ባልደረቦቹ ፣ተማሪዎቹ እና አገልግሎቱን ያገኙ ደምበኞቹ የሚመሰክሩለት ድንቅ ሃኪም የነበረ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል።
በመሆኑም ፦
➡️ የዶ/ር አንዱአለም ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ሲደርሱ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በነጻ እንዲማሩ፤
➡️ ባለቤቱ ከትምህርት ዝግጅት አንጻር በሲቪል ምህንድስና 2ኛ ዲግሪ ያላት እና ጥሩ አቅም ያላት በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የምትቀጠርበት ሁኔታ እንዲመቻች፤
➡️ ዶ/ር እንዱአለም በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታሪክ የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና የሰራው እሱ በመሆኑና ክፍሉን እስከ ህልፈቱ ድረስ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረ በመሆኑ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ዋርድ በስሙ ዶ/ር አንዱአለም ዳኘ ቀዶ ጥገና ዋርድ ተብሎ እንዲሰየም፤
➡️ የዶ/ር አንዱአለምን የአገልጋይነት ጥግ እንዲሁም ለሙያው የተሰጠ ተምሳሌታዊነቱን በቋሚነት ለመዘከርና ማስተማሪያ እንዲሆን በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ሃውልት እንዲቆምለት፤
➡️ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ School of Medicine ውስጥ በስሙ BDU Talent Scholarship እንዲቋቋም፤
➡️ ለ40ኛ ቀኑ መታሰቢያ የሚደርስ ስለ ዶ/ር አንዱአለም የህይዎት ታሪክ የሚዳስስ መጣጥፍ እንዲዘጋጅ ዩኒቨርሲቲው ወስኗል።
ውሳኔው ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት ቀርቦ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡