” ሀኪም ህይወት እያተረፈ ፣ህይወቱን መነጠቅ የለበትም! ” – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ዶ/ር አንዷለም ዳኜ ከስራ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲመለስ በጥይት ተደብድቦ በመገደሉ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና መላው የሃገራችን ህዝቦች በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ፍትህን በመጠየቅ ላይ ናቸው።

” ፍትህን እንሻለን ! ” በሚል የፍትህ ጥያቄ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አሳውቋል።
የዶ/ር አንዷለም ዳኜ ሐዘን በማስመልከት ፍትህ ጥያቄ በተማሪዎችና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የቀረበበት የሀዘን ምሽት በጥበበ ግዮን ግቢ መካሄዱ ተገልጿል።
➡️ ለሃኪሞቻችን ጥበቃ ይደረግልን፤
➡️ አዳኙ ፣ አካሚው ሃኪም ለምን ተገደለ ፤
➡️ አትግደሉን፣
➡️ መድሃኒቱ ሃኪም ጥይት አይገባውም ወዘተ የሚሉ መፈክሮችና የፍትህ ጥያቄ አዘል ምልዕክቶች በስራ ባልደረቦቹ፣ በተማሪዎቹ እና በወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ቀርበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ” አንድን ትልቅ ሃኪም ቀብሮ ገብቶ ዝም ማለት እንደ ዩኒቨርሲቲ ከብዶናል ” ብሏል።

” የተገደለብን፣ የተነጠቅነው፣ በርካታ የሆስፒታላችን ደንበኞች ፣ ህሙማን እንዲያድናቸው በወረፋ ቀጠሮ ይዘው የሚጠብቁትን የህዝብ ተስፋ፤ የአገር አንጡራ ሃብት ፣ ኢትዮጵያ ሃገራችን ሰፊ ሃብት ያፈሰሰችበትን ወጣት ሰብ ስፔሻሊስት ሃኪም ነው፡፡ ፍትህ መጠየቃችንን እንቀጥላለን ! ” ሲል አክሏል።
ሁሉም የፍትህ ጥያቄ ዘመቻውን እዲቀላቀል ጥሪ ቀርቧል።
ይኸው ከቀናት በኃላ እንኳን ዶክተር አንዷለም ዳኜን ስለገደሉ አካላት ምንም በይፋ የተነገረ ነገር የለም።