” ከፕሬዜዳንቱ እና ካቢኔው በላይ የሆነ የማይታዘዝ ሃይል ተፈጥሯል “- አቶ ብርሃነ ገ/ኢየሱስ
በትግራይ ከጊዚያዊ አስተዳደር ” ከፕሬዜዳንቱ እና ከካቢኔው በላይ የሆነ የማይታዘዝ ሃይል ተፈጥሯል ” ሲሉ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙት የመቐለ ከንቲባ ብርሃነ ገ/ኢየሱስ ተናገሩ።

” ጊዚያዊ አስተዳደሩ በግልፅ ባያውጅም መቐለ ጨምሮ በመላ ትግራይ በስሙ መጠራት ያለበት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አለ ” በማለት አክለዋል።
ከህዳር 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ የመቐለ ከንቲባ ሆነው በጊዚያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ የተሾሙት እና ህዳር 23/2017 ዓ.ም አንድ ጊዜ ብቻ ቢሯቸው ከገቡ በኋላ ያልተመለሱት ከንቲባው ” ላዛ ትግርኛ ” ለተባለ ሚድያ ሰፊ ቃለመጠየቅ ሰጥተዋል።
” ወታደራዊ ሃይል በመጠቀም ከመንግስት በላይ ሆኖ ከንቲባ ስራውን እንዳይሰራ ፤ ህዝብ ከከንቲባ ማግኘት ያለበት አገልግሎት እንዳያገኝ መከልከል የህግ ተጠያቂነት ከማስከተል በተጨማሪ በታሪክ ያስወቅሳል ” ብለዋል።
ከ8 ወራት በፊት ሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ዞን ፤ ከ4 ወራት በፊት ማእከላዊ ዞን እንዲያስተዳድሩ በጊዚያዊ መንግስት ፕሬዜዳንት ፊርማ የተመደቡ ሃላፊዎች ተግባራቸው እንዳይፈፅሙ ስሙ ባልጠቀሱት ወታደራዊ አዛዥ የሚታዘዙ ጠበንጃ ባነገቡ ታጣቂዎች እንደተስተጓጎሉ ጠቅሰዋል።
እሳቸውም ” ከፓሊሰ አቅም በላይ ያልሆነውን ጉዳይ የመቐለ አስተዳደር ዙሪያ በታጣቂዎች በማጠር ወደ ቢሮ እንዳይገቡ ከሁለት ወር በላይ መከልከላቸው እጅግ አሳዛኝ እና የመንግሰት ትእዛዝ የጣሰ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ” ብለዋል።
ፕሬዜዳንቱና ካቢኔው ሦስት ጊዜ ወደ ስራ ገበታቸው ገብተው ስራቸው እንዲሰሩ ቢያዝም አስተዳደሩን እንዲጠብቁ በታዘዙ ታጣቂዎች መከልከላቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው እና እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል።
” መንግስት መንግስት መምሰል አለበት ትእዛዝ እና ውሳኔ በማክበር እና በማስከበር ከመንግስት በላይ መሆን የሚፈልገውን አካል ማቆምን ማስታገስ ይገባዋል ” ብለዋል።
” ከፕሬዜዳንት እና ከካቢኔ በላይ በመሆን ታጣቂዎች በአስተዳደሩ ዙሪያ ያስቀመጠ አካል የወጣቶች ቁጣ እና መልእክት ተቀብሎ ያሰማራቸው ታጣቂዎች በአስቸኳይ ማንሳት አለበት ” ያሉት ከንቲባው ” ጉዳዩ ፓሊስን ይመለከታል ከፓሊስ አቅም በላይ ከሆነ የአድማ ብተና ሃይል ይሰማራል ፤ ከዚህ ውጭ ከአቅሜ በላይ ሆኗል የሚል ጥያቄ ባልቀረበበት ታጣቂ ሰራዊት ማስቀመጥ ከህግ በላይ መሆንን ያመለክታል ” ሲሉ ስሙ ያልጠቀሱት ታጣቂዎች አሰማርተዋል ያሉትን አካል ተችተዋል።
መቐለ ካሉዋት 7 ክፍለ ከተሞች እና 33 ቀበሌዎች ዙሪያዋ የተወጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አደባባይ በመውጣት ከንቲባ ስራውን እንዲጀምር ፤ ህዝቡ መንግስታዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ፤ የጊዚያዊ አስዳደሩ ትእዛዝ እንዲከበር ድምፃቸው አስምተዋል ያሉት ከንቲባ ብርሃነ ” አሁንም መልስ ካላገኙ ከበፊት በላቀ ቁጥር ወጥተው ድምፃቸው ማሰማታቸው ይቀጥላሉ ” ሲሉ ዝተዋል።
መቼ ወደ ተመደቡበት ስራ እንደሚገቡት ለቀረበላቸው ጥያቄ የተቆረጠ ቀን እንደማያወቁ ተናግረዋል።
” ትግራይ ከገባችበት ፓለቲካዊ ቀውስ የምትወጣበት እንዱ እና ዋነኛ መንገድ መንግስት ሲኖራት የመንግስት ትእዛዝ እና ውሳኔ ሲከበሩ ነው ስለሆነም ከህግ እና መንግስት በላይ በመሆን ታጣቂ ያሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው ይቆጠቡ ” ሲሉ አሳስበዋል።
በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት እና በጊዚያዊ አስተዳደሩ የተመደቡላት ከንቲባዎች ከስራ ውጭ ሆኖዉባት ከንቲባ ያጣቸው የትግራይ የፓለቲካ እና የኢኮኖሚ ከተማ የሆነችው መቐለ የከንቲባዋ ፅህፈት ‘ታሽገዋል ‘ የሚል ወረቀት ተለጥፎለት በግራና ቀኝ በቆሙ ፓሊሶች እንዲሁም ዙሪያዋ በታጣቂዎች ለ24 ሰዓት መጠበቅ ከጀመረች 64 ቀናት ተቆጥረዋል ሲል የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ መረጃውን አድርሶናል።