አሜሪካ፣ ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎችን ተቀብላ እንድታሠፍር ለማግባባት የሕዳሴ ግድብ ውዝግብን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት መኾኑን ከዲፕሎማቲክ ምንጮች መስማቱን ጠቅሶ ኒው ዓረብ ድረገጽ ዘግቧል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ልዑካን ሰሞኑን ወደ ካይሮ ባቀኑበት ወቅት፣ ከግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባደር አብደላቲና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በዚኹ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተው እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል።
የሕዳሴው ግድብ ውዝግብን ለመፍታት አሜሪካ ገንቢ ሚና እንድትጫወት ከተፈለገ፣ ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎችን ተቀብላ ማስፈር እንዳለባት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለግብጽ አቻዎቻቸው ነግረዋቸዋል ተብሏል።
ግብጽ ግን ከፊል የጋዛ ነዋሪዎችን እንድታሠፍር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ሃሳብ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው፣ የግድቡን ውዝግብ ለመፍታት ያቀረቡትን አስገዳጅ የሦስትዮሽ የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።