ከሻቢያ የተጠጋ ሁሉ መጨረሻው ክሽፈት፣ ውርደትና ውድመት ነው፤ ( ያሬድ ሃይለማርያም፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
+++++
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሻቢያን እጁን ይዘው እየጎተቱ ጣልቃ የሚያስገቡና አቅም ባነሳቸው ቁጥር ኢሳያስ እግር ስር የሚነጠፉ ፖለቲከኞች ሁሌም መጨረሻቸው ኢትዮጵያን እንዳዋረዷት፣ እንደጎዷትና እንዳከሰሯት ነው። ኢሳያስ የራሱን ሀገር ኤርትራን ያቆረቆዘ፣ የኤርትራን ወጣት በባህር ያሰደደና ለባህር አውሬ የዳረገ፣ ሕዝቡንም አፍኖ ይዞ ያደኸየ ክፉና በቀጠናው ውስጥ ከቀሩ አንጋፋ ጨካኝ አንባገነኖች አንዱ ነው። ኢሳያስ የነካው የኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉ ሁሌም ውድመትና ምን እንደነካው እንጨት መጨረሻው አስከፊ መሆኑን እንዴት ወደኋላ መለስ ብለው ማየት እንደሚቸገሩ ግራ ይገባኛል።
1ኛ/ ወያኔ ከጫካ ወደ ስልጣን ስትመጣ ሻቢያን ከፊት አስቀድማ ነበር። አዲስ አበባን ተቆጣጥራም ለተወሰኑ ጊዜያት ቤተመንግስቱ ጭምር ይጠበቅ የነበረው በሻቢ ጦር ነበር። ኤርትራም ስትገነጠል ህውሃት ዋነኛ ሂደቱን አቀላጣፊ በመሆን ኢትዮጵያን የሯሷን አገር ለማስገንጠል የእውቅና ደብዳቤ የጻፈች የመጀመሪያዋ አገር አረገቻት። መለስ ከሻቢያ የበለጠ አሰብንም ውሰዱልኝ ብሎ መሸኘቱን አደራዳሪዎቹ መስክረዋል። ሻቢያ ግን በዛም ሳያበቃ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ እቅድና ስልት ነድፎ ጠላትነቱን አጠናክሮ ቀጠለ።
2ኛ/ ከዛም ባለፈ ወያሬ የአገሪቱን አንጡራ ሃብትና ከቡና እስከ ጦር መሣሪያ ጭምር በሻቢያ እንዲዘረፍ ሁኔታዎችን አመቻቸችለት። ውለታዋን ግን ሻቢያ ባድመንና ዛላንበሳን በመውረር በክህደትና በጭካኔ ሳይል ሳያድር መለሰ። ብዙ ሺዎች አለቁ። ትግራይ ዳግም በደም ጨቀየች። ሻቢያ ዋና የህውሃትና የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ቀጠለ።
3ኛ/ ከወያኔ መማር ያልቻሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ወያኔ አስከፍታናለች ብለው ኢሳያስ እንዲያስጠልላቸው፣ እንዲያስታጥቃቸው፣ እንዲያሰለጥናቸውና መልሰው ኢትዮጵያን ለመውጋት አጋር እንዲሆናቸው እግሩ ላይ ተጠነፉ። ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር፣ ግንቦት 7 እና ሌሎችም የትግራይ ታጣቂዎች ኤርትራ በርሃ ገቡ። በተለይም የግንቦት 7 አመራሮች፤ አንባገነናዊ ሥርአትን እንዋጋለን ብለው ጫካ የገቡት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና አመራሮቻቸው ፕሬዚደንት ኢሳያስን ከመላዕክት ተርታ ሊያስቀምጧቸው ምንም አልቀራቸውም ነበር። የፕሮፖ ጋንዳ ማሽናቸው በነበረው ኢሳት ሚዲያ ኢሳያስን ማቆለፖፐስ ብቻ ሳይሆን ኢሳያስን የሚመለከቱ ክፉ ነገሮችና ዘገባዎች እንዳይሰሩም ይደረግ ነበር። እርግጥ ደሞዝ ከፋያቸው፣ አልባሽ፣ አስጠላያቸው ስለነበሩ አይገርምም። ግን ከምሁርና ከነጻነት ታጋዮች የማይጠበቅ መርህ አልባ የሆነ ገጸ ባህሪ ይዘው ለአመታት የኢሳያስ ደንገ ጡር ሆነው ነበር። “ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ” የሚል መጽሐፍን ጽፎ ያሳተመ ሰው ከኢሳያስ ጎን ይሰለፋል ብሎ ማሰብ ለብዙዎቻችን ከባድ ነበር። ኤርትራ በርሃ ለአመታት የመሸጉት ታጣቂዎች አንድሞ የአገሪቱን የጠረፍ መንደር እንኳ ሳይቆጣጠሩ መሣሪያ ያልታጠቁ የኦሮሞና እና የአማራ ወጣቶች ወያኔን በባዶ እጅ ተፋልመው ባመጡት ድልና ነጻነት ኤርትራ የመሸጉ ሀይሎች ጀሌዎቻቸውን እያንጋጉ አዲስ አበባን እንዲረግጡ በር ከፈቱላቸው። የኦነግ እና የግንቦት 7 መሪዎች በቦሌ አየር ማረፊያ ገብተው አብዬት አደባባይ ሲረግጡና ስታዲዬም ውስጥ በደስታ የፈነጠዙት ኢሳያስ እረድቷቸው አልነበረም። የቄሮ ንቅኔቄ ባይፈጠር ኖሮ ሁሉም ይሄኔ እዛው አስመራ ቁጭ ብለው ከኢሳያስ ጋር የአዛውንት ጭራቸውን እያወዛወዙ ቡና እየጠጡ በኢሳት መንግስትን ይራገሙ ነበር።
4ኛ/ ከወያኔም፣ ከግንቦት 7 እና ከኦነግም የሻቢያ ወዳጅነት ምንም ትምህርት ያልወሰደው ልጅ አብይ አህመድ በግንቦት 7 መሪዎች መንገድ እየተመራ ትንሽ የማሰላሰያ ጊዜ እንኳ ሳያጠፋ ሰላም ወዳድ በመምሰል እየተቅበዘበዘ በትግራይ አናት ላይ ተረማምዶ ከኢሳያስ ጋር በፍቅር ሽር ብትን ሲል የተወሰንን ሰዎች ይሄ መርህ አልባ የሆነ አካሄድ አደጋ እንዳለው ሳይውል ሳያድር ጠቁመን ነበር። አብይ የፖለቲካ እንጭጭነቱ ይበልጥ ጎልቶ የታየውም ያኔ ኢሳያስን ሲያገኘው የሚያሳያቸው ባህሪያት ነበሩ። አንድን ትልቅ አገር ከሚመራ ሰው የማይጠበቁ የተለማማጭነት፣ የመነጠፍ፣ የአድር ባይነት ባህሪ አለምን አስደምሞ አልፏል። የመሪነትን ፕሮቶኮል ባልጠበቀ መልኩ እጅ መሳም፣ ቀለበት አውልቆ መስጠት፣ ሹፌር ካልሆንኩ ማለት፣ የጃኖ፣ ካባ ጋጋታ እና ፈረስ ጭምር መሸለም ብዙ የዋሆች የአብይን ትሁትነትና አክባሪነት ማሳያ ቢያደርጉትም ነገሩን በጥንቃቄ ላየው ግን የማነስ፣ የመነጠፍ፣ የካድሬነት፣ የአስመሳይነት፣ populist የመሆን በሽታ መገለጫ ነበር። የአብይ ክሽፈት በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር። ከህውሃት ጀርባ ትግራይን ዘሎ ከሻቢያ ጋር መሞዳሞዱ ምን መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ የመረዳት አቅም ያጣው ወይም ሆን ብሎ የተሰላ የክፋት መንገድን የመረጠው አብይ ከወያኔ ጋር ሲጣላ ኢሳያስን እጁን ስቦ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በማስገባት በታሪካችን አይተነውና ሰምተነው የማናውቀውን እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላው ጭፍጨፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ አስፈጸመ። ወያኔን ለመበቀል አድፍጦ ጊዜ ይጠብቅ የነበረው ሻቢያ ጦሩን ይዞ እስከ መሀል ትግራይ በመግባት ህውሃትን ሳይሆን የትግራይን ሕዝብ ዘርፎ፣ ጨፍጭፎ፣ ከአዋቂ እስከ ህጻን ደፍሮ ሄደ። በወቅቱ የሻቢያን ጣልቃ መግባ ስንቃወም አብይና ጭፍን ደጋፊዎቹ ይሳለቁ ነበር።
5ኛ/ ሻቢያ ከኢትዮጵያ ጋር መቸም ሰላም ሆኖ መቀጠል የማይችል የእድሜ ልክ የወገብ ውጋት እንደሆነ ማሳያው ከመርህ አልባው አብይ ጋር ለመጣላት ጊዜ አለማጥፋቱ ነው። የፊት የፊቱን ብቻ እያየ የሚደናበረው አብይ የፕሪቶሪያን ስምምነት ሲፈርም ከኢሳያስ ጋር የሚኖረውን ወዳጅነት እና የወንጀል ተጋሪነት እንዴት ማስቀጠል ወይም በጥንቃቄ ማቆም እንደሚችል እውቀቱ ስላልነበረው ከኢሳያስ ጋር ለመላተም ጊዜ አልወሰደበትም። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ሻቢያ በትግራይ ላይ ለፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋና የበቀል እርምቻ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን በመሪነት በመፈጸም አብይ በከባድ የጦር ወንጀልና በአገር ክህደትም ጭምር ሊጠየቅ የሚገባው ሰው መሆኑን ነው።
6ኛ/ ዛሬ ለቅሶው እና ውንጀላው ተቀይሮ አብይ ህውሃትን እና ፋኖን ከሻቢያ ጋር በማበር ሊወጉኝ ነው የሚል ነጠላ ዘማ ሰሞኑን ለቋል። ከኤርትራ ጋር የሚሰሩ ሁሉ ባንዳዎች ናቸው እያለ ነው። አንቺን ሲልሽ ሲልሽ ትመጫለሽ በረሽ፤ እኔን ሲለኝ ሲለኝ … የሚለውን ግጥም ማስታወስ ይሄኔ ነው።
7ኛ/ ሰሞኑን ከህውሃት ሰዎች እና ከአንዳንድ የፋኖ አመራሮች ከኤርትራ ጋር መተባበር እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። አንዳንድ የትብብር ምልክቶችም እየታዩ ነው። ለእነዚህ ሃይሎች ያለኝ ምክር እባካችሁ ከወያኔ፣ ከግንቦት 7፣ ከኦነግ፣ ከብልጽግና ክሽፈት ትምህርት ወስዳችሁ ከኢሳያስ ጋር የጀመራችሁት ትብብርም ሆነ ማናቸውም መደጋገፍ ካለ አቁሙ። በእውነት ኢትዮጵያን የምትወዱና የምትታገሉትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም የእኔ ለምትሉት ሕዝብ ከሆነ ኢሳያስ የነካው ነገር መዘዙ ብዙና መውጫም ስለሌለው አትግቡበት። የሩቁን ትታችሁ ከአብይ ክሽፈት ተምራችሁ ከኢሳያስ ነጻ ሁኑ።
ትግሉ ሊረዝምባችሁ ይችላል፣ አቅም ሊያንሳችሁም ይችላል ግን ምንም ቢሆን ኢትዮጵያን በዘለቄታው የግጭት ቀጠና እንድትሆን ከግብጽና ሌሎች ጸረ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ሃይሎች ገንዘብ እየተቀበለ ትግላችሁን ልደግፍ ከሚለው አንባገነኑ ኢሳያስ በመራቅ ለአገራችሁም ለሕዝባችሁም ውለታ ዋሉ። ኢሳያስ የደቀቀ አገርና ኢኮኖሚ ይዞ የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ሃይሎች የሚረዳው በግብጽ በጀት ነው። ለዚህ የዛሬው ትምህርት ሚኒስትር የትላንቱ የግንቦት 7 አርበኛ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ባልደረቦቹ ጥሩ ምስክሮች ናቸው። የግንቦት 7 አመራሮች መቀመጫቸውና መዶለቻቸው አስመራና ካየይሮ ነበር። ትልቁን በጀታቸው የሚትሸፈነው በግብጽና በኤርትሬ በኩል በሚላክ የግብጽ ገንዘብ ነበር። የግንቦት 7 አመራሮችም ምን በበላበት ይጮኻል እንደሚባለው ዛሬ እያጨበጨቡ ያስመረቁት አባይ ሲገደብ ከግብጽ እኩል ይጮኹና ይቃወሙ ነበር።
ለማንኛውም የባንዳ አዙሪት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች፤ ደርግ ወያኔን ባንዳ ይል ነበር። የሻቢያ አጋር የነበረው ወያኔ ደግሞ በተራው እነ ግንቦት 7ን ባንዳዎቾ ይል ነበር። የዛሬ ሦስትና አራት አመት ግድም የባንዳነት ማሊያውን አጥልቆ በአጥቂነት ቦታ ተሰልፎ የነበረው ብልጽግና ዛሬ ህውሃትን፣ ፋኖንና ሽኔን ባንዳዎች እያለ ነው።
የባናዳነት ማሊያውን የለበሱ ፖለቲከኞች ሁሉ ከሽፈዋል፣ አገር አዋርደዋል። አዲሶቹ ሃይሎች ያንን ስህተት እንዳትፈጽሙ ለመማጸን ነው ይሄን ዘለግ ያለ መልዕክት የየጻፍኩት።
ኢሳያስ የገዛ ሕዝቡን የበደለ ክፉ አንባገነን ሰው ለኢትዮጵያ ምን ሊበጃት ነው?
ወያኔ፣ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ብልጽግና ያጠለቁት የባንዳነት ማሊያ ህውሃትም፣ ፋኖም፣ ሽኔም ቢያጠልቁት ውጤቱ ያው ነው። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሻቢያን ማስገባት ሁሌም ቢሆን የአገር ክህደት ነው።