በአፋብኃ ምስራቅ አማራ ምኒልክ ዕዝ መስከረም 14/2018 ዓ.ም የተጀመረው ዘመቻ አርበኛ አደም አሊ (አባ ናደው) በበርካታ ወታደራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ታጅቦ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተቋጭቷል::
ዘመቻው፣ መስከረም 14/2018 ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት በአምስቱም ኮሮች በተመሳሳይ ሰዓት ውጊያ በመክፈት ከጀመርንበት ቅጽበት አንስቶ የአፋብኃ ምኒልክ ዕዝ፡-
ምስራቅ አማራ ኮር 1፣ ምስራቅ አማራ ኮር 2፣ ላስታ አሳምነው ኮር፣ ልጅ ዕያሱ ኮር፣ ንጉስ ሚካኤል አሊ ኮር፣ የዕዙ ልዩ ዘመቻ እንዲሁም በአንዳንድ ቀጠናዎች በቅንጅት የድርጅታችን አካል የሆኑት ቴዎድሮስ ዕዝ፣ አሳምነው ዕዝ፣ በላይ ዘለቀ ዕዝ እና መላው የሰራዊታችን አባል፣ በየደረጃው የሚገኙ የኃይል አመራሮች እና የዕዛችን ሥራ አስፈጻሚ አመራሮች 24/7 እረፍት አልባ የውጊያ ተሳትፎና አመራር በመስጠት የኀልውና ትግሉን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ማስገባት ተችሏል፡፡
ዘመቻው ታቅዶ ወደተግባር ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ የድርጅታችን አፋብኃ ቀጠናዊ አመራሮች የሞራል ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ፤ የዘመቻው አካል በመሆን የጠላትን እንቅስቃሴ በመገደብ አልፎም ባደረግናቸው የጋራ ውጊያዎች፣ የአማራ ሕዝብ የኀልውና ትግል መሪ ድርጅት እንደተፈጠረ በተግባር አሳይተናል፡፡
ለ18 ቀናት ያለ እረፍት በዘለቀው ዘመቻ አባ ናደው በርካታ የነፍስ ወከፍ የቡድንና መካናይዝድ ጦር መሳሪያዎችን ከበርካታ ተተኳሽ ጋር እንዲሁም ከ20 በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪ በምርኮ የተገኘበት ሲሆን፤ ጠላት አምስት ክፍለጦሮቹ የተበተኑበት፤ ውጊያን አቅደው የሚመሩ የውጊያ መሃንዲሶቹን ጨምሮ በርካታ መስመራዊ መኮንኖቹን ያጣበት፤ በመቶዎች የተማረኩበትና በሽዎች ሙትና ቁስለኛ የሆነበት ስኬታማ ዘመቻ እንደነበር በግምገማችን አረጋግጠናል፡፡
የአማራ የኀልውና ትግል ከጀመረበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ጠላት ካስተናገዳቸው ኪሳራዎቹ እጅግ የከበደውን ኪሳራ በዘመቻ አደም አሊ አስተናግዷል፡፡
ፋኖ በርካታ ወረዳዎችን፣ ከተማ አስተዳደሮችንና ሰፊ ቀጠና የተቆጣጠረበት፣ የህዝብ አስተዳደር መዋቅር በሰፊው የዘረጋበት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም በቀጣይ እንደ አማራ፣ አፋብኃ በሚያውጀው ዘመቻ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ትልቅ ፍንጭ የሰጠንበት አቅማችንን ለወዳጅ ጠላት ያሳየንበት ልዩ ዘመቻ ነበር፡፡
በጥቅል ግምገማችን በዘመቻው የፋኖ የኀልውና ትግል አዲስ የትግል ምዕራፍ የደረሰበት በመሆኑ በተመዘገበው ድል ሰራዊታችንና ድርጅታችን ብቻ ሳይሆን የትግሉ ባለቤት የሆነው መላው የአማራ ሕዝብና የአማራ ትግል ደጋፊዎች እንኳን ደስ አለን! እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡
ከምንም በላይ የአማራ ፋኖ ትግል ዓለማቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንደሚያከብር፣ በምርኮኛ አያያዙ ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በማሳየት ትግላችን ራስን የመከላከል፣ እንዲጠፋ የተፈረደበትን ሕዝብ ኀልውና የማዳን ተልዕኮ እንደሆነ በተግባር ማስመስከር ችለናል፡፡
ነፃ በወጡ ከተሞችና የወረዳ ማዕከላት ደማቅ አቀባበል ያደረገልን ሕዝባችን፣ በተሳትፎው የትግሉ ባለቤትነቱን ዳግም አስመስክሯል!!
የአለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ (International humanitarian law) በሚደነግገው መሠረት ሰብዓዊ ክብራቸውን በጠበቀ ሁኔታ የያዝናቸው የቀድሞ የብልጽግና ሰራዊት አባላት ይህን ምስክራቸውን በዓለማቀፉ ማኀበረሰብ አባላት ፊት መስክረዋል፡፡ ይህ አዲሱ የአማራ ኀልውና ትግል የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡
በቀጣይም እንደ ድርጅት በምናደርጋቸው ዘመቻዎች ለአለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ ተገዢ ሆነን እስከ አራት ኪሎ ድረስ እንደምንዘልቅ ዳግም ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
አጠቃላይ ባለፉት 18 ቀናት በዘመቻ አባ ናደው የተመዘገቡ ዝርዝር ቁጥራዊና ሌሎች መረጃዎችን የማጠቃለያ ሪፖርትን ይዘን እንመለሳለን!
መዳረሻው ድልና ነፃነት የሆነው የአማራ ህዝብ የህልዉና ተጋድሎ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
ኀልውናችን በተባበረ ክንዳችን!
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ