የሻዕቢያ እና የብልፅግና እርስ በርስ የቃላት ትችት ቀጥሏል

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል፣ የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ሰኞ’ለት ለኹለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር ላይ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በብሉ ናይል እና ቀይ ባሕር ላይ ያንጸባረቀው ትርክት “ግራ የሚያጋባ” እና “ለማሰብ የሚከብድ” ነው በማለት ተችተዋል።

የማነ፣ በብሉ ናይል እና በቀይ ባሕር አጀንዳዎች መካከል ከጅዖግራፊያዊ ግንኙነት፣ ከሕጋዊ ንጽጽር ወይም ከጅዖፖለቲካ ተመጣጣኝነት አንጻር አንዳችም ተመሳሳይነት የለም ብለዋል።

የማነ “ቅዠት” ሲሉ የጠሩት ብልጽግና ፓርቲ በቀይ ባሕር ላይ የሚያራምደው ትርክት፣ በብዙ ነውጦችና ችግሮች በሚታመሠው ቀጠና ውስጥ “አላስፈላጊ” እና “ሊወገድ የሚችል” ግጭት የሚቀስቀስ ይዘት ባይኖረው ኖሮ፣ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እና እንደማይረባ “ቅዠት” ቆጥሮ መተው ይቻል ነበር በማለት አጣጥለዋል።