ከአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር ለፋኖ ኃይሎች የተሰጠ የአጋርነት መግለጫ

ከአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር ለፋኖ ኃይሎች የተሰጠ የአጋርነት መግለጫ!

የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር ከሰሞኑ በአማራ ክልል ወሎ ግንባር በአገዛዙና በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ በኩል እየተደረጉ ያሉ ውጊያዎችን በትኩረት እየተከታተለ ይገኛል።

የፋኖ ኃይሎች ከባዶ እጅ በመነሳት ዛሬ ላይ በመካናይዝድ የታገዘ መደበኛ ውጊያ እያደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል። የተሰየመው ዘመቻም ዘመቻ አደም አሊ የሚል መሆኑን፣ ዘመቻው የተሰየመለት ፋኖ፣ በትግል ላይ የተሰዋ ሙስሊም ፋኖ መሆኑንም አረጋግጠናል።

ይህ የፋኖ ኃይሎችን የአንድ ኃይማኖት ሰዎች ናቸው፣ የቀድሞውን ሥርዓት ለመመለስ ነው የሚታገሉ የሚለውን የብልጽግና አገዛዝ የሐሰት ፍረጃ፣ እንዲሁም በፍረጃው ለተሳሳቱ ሁሉ ምላሽ የሚሰጥ ሁኖ አግንተነዋል።

የፋኖ ኃይሎች እያደረጉ ላለው ከባድ ትግል እውቅና የምንሰጥ መሆኑን እንገልጻለን።

የአማራ ሕዝብና የአፋር ሕዝብ ከትናንት እስከዛሬ በመከራም፣ በደስታም የጋራ እጣ ፈንታ ያላቸው መሆኑ ይታወቃል። አሁን ላይ በአብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ተቀባይነት የሌለውና ለሀገር ወዳዱ የአማራ ሕዝብም ይሄ የማይገባው መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች እያደረጉት ያለው ተጋድሎ ከነሱም መግለጫዎች በተደጋጋሚ እንደተረዳነው የመላው ኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ነጻነት እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል።

እኛም የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር በቀጣይ ከፋኖ ኃይሎች ጋር በጋራ በመታገል የአብይ አህመዱን የብልጽግና አገዛዝ ለአንዴና ከመጨረሻ ጊዜ በመጣል በእኩልነት የጋራ አገር ለመገንባት በትብብር እንደምንሰራ ስንገልጽ በደስታ ነው።

በመጨረሻም አፋርን እንደመሸጋገሪያ በማድረግ የአማራ ሕዝብን ለማውድም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መላው የአፋር ሕዝብ እንዲቃወምና እንዲያስቆም የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር ይጠይቃል፣ እንዲቆም እንደምንሰራ መግለጽ እንፈልጋለን።

መላው የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የትግል መነሻዎቻችን ተረድቶ በሀገራችን ላይ የተደቀነው ብሄራዊ አደጋ በጋራ ትግል እንዲቀለብስ ጥሪ እናቀርባለን።

ግመሎቻችን ጭምር የሚያውቋት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዳትወድቅ፣ ነፃ ሀገር እንድትኖረን ለትግላችን አስፈላጊውች ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን !

ድልና ድምቀት ለአፋር ኡጉጉሞ!