የአዲስ አበባ ፖሊስ ነዋሪዎችን በዘፈቀደ ካሠረ በኋላ በነፍስ ወከፍ 2 ሺሕ ብር እየተቀበለ ነው

የአዲስ አበባ ፖሊስ የደኅንነት ስጋት ትፈጥራላችኹ በሚል ጠርጥሬያቸዋለኹ ያላቸውን ነዋሪዎች በዘፈቀደ ካሠረ በኋላ በነፍስ ወከፍ 2 ሺሕ ብር እየተቀበለ እንደሚለቅ ታስረው ከተፈቱ ሰዎች ተናገሩ።

ባለፈው ቅዳሜ ገርጂ አካባቢ ከታሠሩ 50 ወጣቶች መካከል፣ ስድስቱ በነፍስ ወከፍ 2 ሺሕ ብር ከፍለው መለቀቃቸው  ታውቋል ።

ገንዘቡን መክፈል አንችልም ያሉ ወጣቶች፣ ለአራት ቀናት ከታሠሩ በኋላ ፖሊስ ጣቢያውን የሚጎበኙ ዓቃቢያነ ሕግ እንደሚመጡ ሲታወቅ እንደተለቀቁ ተናግረዋል።

ገንዘቡ የሚከፈለው በደረሰኝ ሳይኾን፣ ለተረኛ ፖሊሶች በጉቦ መልክ የሚከፈል ነው ተብሏል።

 በጉዳዩ ዙሪያ የከተማዋን ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሠ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት  አልተሳካም።