
በአማራ ክልል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን የተሰራ ርብራብ እንጨት ተደርሞሶ የ30 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
መረጃውን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዣዥ ዋና ኢንስፔክተር አሕመድ ገበየሁ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነግረውታል፡፡
የአደጋው ምክንያት ለቤተክርስቲያኑ ሕንጻ ግንባታ በተሠራ የእንጨት መወጣጫ ርብራብ ላይ መሸከም ከሚችለው በላይ ሰዎች ለጉብኝት በመውጣታቸው ነው ብለዋል።
በአደጋው የ30 ሰዎች ሕይዎት ወዲያውኑ አልፏል ሲሉ ዋና ኢንስፔክተር አሕመድ አስረድተዋል።
ከ200 በላይ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲኾን ይህም የሟቾችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአረርቲ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ርብራብ እንጨት ተደርሞሶ ሕይወታቸውን ባጡ ምእመናን የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ግልጸዋል፡፡
“የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ተጠናቆ ምርቃቱን በጉጉት እየጠብቀን ባለንበት ይህ አስከፊ ኀዘን በመከሰቱ ጥልቅ ኃዘን ተሰምቶናል” ብለዋል።
በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን የቅዱሳን አምላክ ነፍሳቸውን በደጋጎቹ ቅዱሳን አባቶቻችን አጠገብ ያሳርፍልን ጉዳት ደርሶባቸው በጤና በሆስፒታል በሕክምና ለሚገኙ ወገኖቻችን ፈጣሪ በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው እንጸልያለን ብለዋል።