ኢትዮጵያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር አበዳሪዎቿ ጋር መደበኛ የእዳ ሽግሽግ ድርድር ጀመረች

 

የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በፊት ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ከዓለም አቀፍ የቦንድ ገዢዎች ጋር የእዳ ሽግሽግ እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው መደበኛ ንግግር መጀመሯን ሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘገበ።

ሮይተርስ ቀደም ብሎ በብሉምበርግ የወጣውን ዘገባ በማረጋገጥ ከዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ጋር በእዳ ሽግሽግ ዙሪያ በፓሪስ ፈረንሳይ ድርድር መጀመሩን ዘግቧል።

አንድ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ዝርዝር መረጃ ሳይጠቅሱ የመንግሥት ልዑክ ወደ ፓሪስ ማቅናቱን አረጋግጠዋል።

“ከቦንድ አበዳሪዎች ጋር የተያዙ አንዳንድ ስብሰባዎች ነበሩ” ሲሉ ለሮይተርስ የተናገሩት ምንጩ የስብስበዎቹ ውጤት መጨረሻ ላይ የሚገለፅ እንደሆነ በመጠቆም ስምምነነት ላይ ግን እንዳልተደረሰ ገልፀዋል።

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ወዲያ ምላሽ አልሰጡም።

የቦንድ አበዳሪዎች ኮሚቴ ተወካዮችም እንዲሁ ምላሽ አልሰጡም።

“ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች” እንደሚውል የተነገረለት የቦንድ ሽያጭ በ10 ዓመታት ተመልሶ የሚከፈል እና የ6.625 በመቶ ወለድ ያለው መሆኑ በወቅቱ ተነግሮ ነበር።

ኢትዮጵያ ያወጣችውን ቦንድ 50 በመቶ የአሜሪካ ባለሃብቶች፣ 35 በመቶ የእንግሊዝ ባለሀብቶች፣ 14 በመቶ የአውሮፓ አገራት ባለሃብቶች እና ሌሎች ገዝተዋል፡፡

በውሉ መሰረት ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም. የቦንድ ብዱሩን ክፍያ መክፈል ያልቻለች ሲሆን፤ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የእዳ ሽግሽግ እንዲደረግ መርጣለች። በዚህ አካሄድ የሁለትዮሽ ብድር፣ ዩሮ ቦንድ እና ሌሎች የንግድ ብድሮች አንድ አይነት አመላለስ አላቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቦንድ ገዥዎች ጋር የእዳ ሽግግር ማድረጊያ መንገዶችን ለመለየት ለወራት ንግግር ሲያደርግ ቆይቷል።

በቦንድ ገዥዎች እና በተበዳሪ መንግሥታት መካከል አሳሪ ያልሆነ ጊዜያዊ ስምምነት መፈረም መደበኛ ድርድር ለመጀመር እንደሚያስችል የጠቀሰው የሮይተርስ ዘገባ፤ በዚህም ሁለቱ ተደራዳሪዎች ተጨባጭ የስምምነት ውል በማሰር እና ድርድሩን ለሦስተኛ ወገን ከማውጣት ይገደባሉ።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ መንግሥት የእዳ ሽግግር ስምምነቱን መደበኛ ማድረጉን ያሳወቀ ሲሆን፤ ገንዘብ ሚኒስቴር 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደሚከፍል አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም ከቦንድ ገዢዎች ጋር የተደረጉ ድርድሮች በተለይም በመንግሥት የመክፈል አቅም ዙሪያ አለመግባባቶች የነበሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አበዳሪዎች ማስተካከያ እንዲያደርጉ ሲወተውት ቆይቷል።

መንግሥት ከዚህ ቀደም የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የብድር ትንተናን በመጥቀስ አበዳሪዎቹ 20 በመቶ ወለድ እንዲቀንሱለት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

ይሁን እንጂ የአበዳሪ ቡድኑ ወኪሎች የአገሪቱን የወጪ ንግድ መረጃ በመጥቀስ ሀሳቡን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፤ የአከፋፈል ጊዜውን ማስተካከል እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

በቅርብ ወራት በመንግሥት ይፋ የሆኑ ጠንካራ የወጪ ንግድ አሃዞች የቦንድ ገዚዎችን ሀሳብ የሚደግፍ ቢሆንም አይኤምኤፍ አነስተኛ ድጋፍ እና የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ነዋይ ፍሰት የክፍያ ትንበያውን ስጋት እንደሚደቅን ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም. ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ መክፈል የነበረባትን ወለድ መክፈል አለመቻሏ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

መንግሥት በቦንድ ሽያጭ ላገኘውን ብድር መክፈል ያልተቻለው በገንዘብ እጥረት እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ሁሉንም አበዳሪዎች “በእኩል ለማስተናገድ” መሆኑን በወቅቱ አስታውቋል።