በሰሜን ወሎ ጤና ጣቢያ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት አራት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 10 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ

የፈራረሰ ሳንቃ ጤና ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት የተፈፀመበት ሳንቃ ጤና ጣቢያ ከፊል ገጽታ

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ቅዳሜ መስከረም 17/2018 ዓ.ም. ጤና ጣቢያ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ የአራት “ሰላማዊ ሰዎች” ሕይወት ሲያልፍ 10 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች እና የሕክምና ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ ከዞኑ እና ከወረዳው ዋና ከተማ ወልዲያ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳንቃ በተባለች የክላስተር ከተማ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ላይ ከቀኑ 06፡00 አካባቢ መፈፀሙን አራት የዓይን እማኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳደር ስለጥቃቱ እና ስለደረሰው ጉዳት ለመናገር እንደማይችል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በስፍራው የነበሩ የጤና ጣቢያው አንድ ባለሙያ መሣሪያው በዋናነት ፊት ለፊት በሆነው እና ታካሚዎች ተኝተው በሚታከሙበት “5 ቁጥር” በተባለው ክፍል ላይ ማረፉን ተናግረዋል።

ከጥቃቱ እንደተረፉ የተናገሩት የጤና ጣቢያው ባልደረባ ጥቃቱ የደረሰበትን ቅፅበት ሲገልፁ “ምንም ራሴን አላውቅም፤ መሬት ተሰንጥቆ የዋጠን ነው የመሰለን። ከጎኔ የነበሩት ሲወድቁ እኔን እግዚአብሔር ነው የከለለኝ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ፍንዳታውን ሰምተው በፍጥነት አካባቢው ላይ መድረሳቸውን የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ጤና ጣቢያው ውስጥ የነበረ የቤተሰብ አባላቸው ከጥቃቱ መትረፉን ገልፀው፤ ዘግናኝ ሁኔታ መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወከባ እና ተጨማሪ የጥቃት ስጋት በመፈጠሩ “በደመ-ነፍስ . . .የደማውም፤ የተመታውም እየተዛዘለ ነው የወጣው” ሲሉ ክስተቱን ተናግረዋል።

የቆሰሉ ሰዎችን ማውጣታቸውን እና አስከሬን ማንሳታቸውን የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ለመግለፅ የሚከብድ ሁነት ማየታቸውን ተናግረዋል።

“ፍንጣሪው እንደ አሽዋ ነው፤ እንደ እሳት ነው የሚያቃጥለው” ያሉት በሕይወት የተረፉ የጤና ጣቢያው ባልደረባ፤ ጤና ጣቢያው ክፉኛ መጎዳቱን ሲገልፁ “ከ5 ቁጥር ጀምሮ እስከ 7 ቁጥር ድረስ የለም” ሲሉ የተቋሙ ክፍሎች መፈራረሳቸውን ገልፀዋል።

ቢቢሲ የተመለከተው እና በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ያልቻላቸውው ፎቶ ግራፎች እና ቪዲዮዎች ጤና ጣቢያው ላይ የደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ።

የጤና ጣቢያው ባለሙያ “ዓይናችን እያየ” አራት ታካሚ እና አስታማሚዎች ሕይወታቸው አልፏል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሦስቱ ልጆቻቸውን ሲያስታምሙ የነበሩ ወላጆች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ሁለት የዓይን እማኞችም በጥቃቱ ሦስት ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን መመልከታቸውን ገልፀው፤ ሟቾቹ “ልጆቻቸውን ሲያስታምሙ” የነበሩ እናት እና አባት እንዲሁም ወደ ሕክምና ከሄዱ በኋላ ሕይወታቸው ያለፉ ለሁለት ወራት በጤና ጣቢያው ተኝቶ እየታከመ የነበረ የአንድ ታካሚ አባት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያው አራተኛዋ ሟች ለመገላገል ጤና ጣቢያ የመጣች ነፍሰ ጡር ሴት መሆኗን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ማዋለጃ ክፍል ላይ የሞተች እናት አለች። አንዷ [ነፍሰ ጡር] ወልዳ ነበር፤ አንደኛዋ እየወለደች እያለች ነው የሞተችው። አሁን ስንሰማ አዋላጅ ነርሱም እጁን ተመትቷል” ብለዋል።

በጥቃቱ የጤና ባለሙያ ልጅ የሆነች የስድስት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ከ10 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም እማኞች ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል ስምንት የሚሆኑት ቁስለኞች የጤና ጣቢያው ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልፀው፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሰኞ ዕለት መንገድ ሲከፈት ቁስለኞች ወደ ወልዲያ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

የጤና ጣቢያውን የጽዳት ሠራተኛ ጨምሮ ስድስት ሰዎች ለሕክምና ወልዲያ ሆስፒታል መግባታቸውን እና ከባድ ጉዳት ያጋጠማቸው ሦስቱ ቁስለኞች ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

በድሮን ጥቃት የደረሰበት የጤና ጣብያው ከፊል ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, በድሮን ጥቃት የደረሰበት የጤና ጣብያው ከፊል ገጽታ

ጥቃቱ ሲፈፀም በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ከተማው ውስጥ ግጭት እንዳልነበረ የገለፁት ነዋሪዎች፤ይሁን እንጂ በወልዲያ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በተለይም ጥቁር ውሃ በተባለው አካባቢ ከባድ ግጭት እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህ ግጭት የቆሰሉ የፋኖ ኃይሎች ሳንቃ ጤና ጣቢያ መግባታቸውን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ አንድ የጤና ባለሙያም “ከ10 የማያንሱ” የፋኖ ታጣቂዎች ቆስለው በጤና ጣቢያው እየታከሙ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የጤና ጣቢያውን ባልደረባ ጨምሮ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጥቃቱ ቆስለው ሕክምና ላይ የነበሩ የፋኖ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

በጥቃቱ ሕክምና ላይ የነበሩ ስድስት ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ የፋኖ ታጣቂዎች እንደተገደሉ እና ቀብራቸውም በአካባቢው እንደተፈፀመ ጠቁመዋል።

ቢቢሲ ስለጥቃቱ የጠየቃቸው የሰሜን ወሎ ዞን የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈለቀ ጌትነት፤ ስለ ጥቃቱም ሆነ ስለደረሰው ጉዳት “ማረጋጥ አንችልም” ብለዋል።

“አሁን አካባቢው ጠላት [የፋኖ ኃይሎች] የሚንቀሳቀስበት ቦታ ነው። እዚያ ላይ ምን ተፈፀመ? ምን ጉዳት አለ? የሚለውን ለማረጋገጥ እኛ ከማኅበረሰቡ መረጃ መሰብሰብ አለብን” ሲሉ ጥቃቱ ስለመፈፀሙም እንኳ መረጋገጥ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሁለቱም የወሎ ዞኖች ዘመቻ መጀመራቸውን እና ድል ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በዋናነት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው ወልዲያ ዙሪያ ላይ ከባድ ግጭት መቀስቀሱን እና እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ተናግረዋል።

አንድ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ በወልዲያ ዙሪያ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች “ተፋጥጠው እንደሚገኙ” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፋኖ ኃይሎች ከፈትነው ያሉትን ዘመቻ “በሚወራው ልክ አይደለም” ሲሉ የተናገሩት አቶ ፈለቀ፤ “ትልቅ መስመር” በሆነው የባሕር ዳር እና ጎንደር መውጫ ጥቁር ውሃ አካባቢ ግጭቶች መከሰታቸውን እና መስመሩ በፋኖ ኃይሎች ለቀናት መዘጋቱን ተናግረዋል።

ከወልዲያ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ሳንቃ ከተማ ሐሙስ መስከረም 15/2018 ዓ.ም. ከሰዓት ጀምሮ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆኗን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሳንቃ አካባቢ ማኅበረሰብም “ከፍተኛ ፍርሃት” ውስጥ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ፈርተን መድኃኒት እንኳ ማውጣት አልቻልንም። ምክንያቱም ድሮን ይዞራል፤ ትናንትም ሲዞር ነው የዋለው። እነሱም [የፋኖ ኃይሎች] እዚህ ናቸው። ምን እንደምንሆን ግራ ገብቶናል” ሲሉ አንድ ነዋሪ ያሉበትን ሁኔታ ገልፀዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ “ሰው ሲወጣ አይታይም፤ አይንቀሳቀስም። በጣም የሚያስፈራ ነው። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።