ጠቅላይ ፍ/ቤት የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች በዋስ እንዲለቀቁ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፀደቀ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት፣ የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በዋስ እንዲለቀቁ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፀደቀ፡፡

የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ፣ጋዜጠኞቹን ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት፣ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው ችሎቱ ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከእስር ቢለቀቁ ማስረጃ ያጠፉብኛል ፣ የሚለውን የፖሊስ ማመልከቻ ባለመቀበል፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ወስኗል፡፡

በሸገር ኤፍ ኤም ጋዜጠኞች አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁንና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው፣ ባለፉት ቀናት፣ የተካሄደው የፍርድ ቤት ውሎ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ነሀሴ 24 ቀን 2017፣ በሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ያቀረቡት የህክምና ባለሙያዎች ፣ ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠውን መፍትሄ ሰርኩላር በመጥቀስ፣ እንዴት እንደሚመለከቱት የሚጠይቅ ዜና ተላልፎ ነበር፡፡

በቃለ መጠየቅ የተደገፈው ዜና፣ “የሽብር ፈጠራ ወንጀል ነው” ብሎ አርታኢዋን ትዕግስት ዘሪሁንና ሪፖርተሯን ምንታምር ፀጋውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ነሐሴ 28/2017 ከመስሪያ ቤት እና ከቤት አግኝቶ በቁጥጥር ስር አዋላቸው፡፡

በማግስቱ፣ ብሔራዊ በዓል በመሆኑ፣ ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት፣ በታሰሩ በሁለተኛ ቀን ነሀሴ 30/2017 ነበር፡፡

ያንለትም ፍርድ ቤቱ፣ በፋይል ብዛት ምክንያት፣ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ ጳጉሜ 3/2017 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
በቀጠሮው ቀን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራና ጋዜጠኞቹ እነ ትዕግስት ዘሪሁን በጠበቃቸው ተወክለው ቀረቡ፡፡

ፖሊስ፣ ጋዜጠኞቹን በቁጥጥር ስር ያዋለበትን ምክንያትና፣ ይቀረኛል የሚላቸውን የምርመራ ሂደቶች፣ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው “በተለያዩ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግር፣ እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሀሰተኛ መረጃና ወሬዎችን በማሰራጨት ፣ በከተሞች በመቀስቀስ ፣ መንግስትና ሕዝብ እርስ በርስ እንዲጋጩ በማድረግ ፣ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን በመሳደብ እና በማስፈራራት ፣ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች በመንቀሳቀስ አመፅ ቀስቃሽ ፅሁፎችንና ቪዲዮችን በመልቀቅ፣ የሃገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ በመቀንሳቀስ እያሉ… ፣ በፀጥታ ሀይል በተደረገው ክትትል ..” በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ስለዚህ የተጠረጠሩበት “የሽብር ወንጀል ድርጊት ውስብስብና የሃገር አንድነትን የሚያፈርስ … በርካታ ስውር የሃገር ማፍረስ ሴራዎች ያለባቸው” መሆኑንና በዋስ ቢለቀቁ የምርመራ ሂደቱን እንደሚያድናቅፉበት ጠቅሶ፣ የ14 ቀናት የምርመራ የማጣሪያ ጊዜ ጠይቋል፡፡

የተጠርጣዎቹ ጠበቃ በበኩሉ፣ ለመታሰራቸው ምክንያት የሆነው ነሐሴ 24 የተሰራጨው ዜና ስህተት አለበት ቢባል እንኳ መታየት ያለበት ለመገናኛ ብዙሃን በወጣው ሕግ መሰረት መሆኑን፣ ማስረጃም በፖሊስ እጅ ያለ መሆኑና ስልኮቻቸውንም ጭምር በእጁ ያስገባ በመሆኑ መረጃ ይደበቃሉ የሚያስብል ምክንያት ስለሌለ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው፣ አመልክቷል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፣ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ለፖሊስ የምርመራ ማጣሪያ ዘጠኝ ቀናት ፈቅዶ ፣ ለመስከረም 7 2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡

በተለዋጩ ቀጠሮ፣ የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቀደም ባለው ቀጠሮ ለፍርድ ቤቱ ያቀረባቸውን ጥርጣሪዎች ቢያሻሽልም ግን “ውስብስብ” በመሆኑ ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

ፖሊስ፣ ከተጠርጣሪዎች የተያዘ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዲመረመሩ፣ ለፎረንሲክ ምርመራ ልኮ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑን ፣ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት የቴክኒክ ማስረጃዎችና፣ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቁን፣ ከተለያዩ የመንግስት የግል ባንኮች የገንዘብ ዝውውራቸው የመጠየቅ ስራ መስራቱን ጠቅሷል፡፡

ነገር ግን የምርመራ ስራውን ለማጠናቀቅ፣ ቀሪ የምስክሮች ቃል የመቀበል ስራ ፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ማግኘት፣ “ተጠርጣሪዎች”፣ ከፀረ ሕዝብና ፅንፈኛ ቡድኖች ጋር ያላቸው ግንኙነት የመለየትና በስፋት የመስራት ስራ እንደሚቀረው ፣ ከባንክ ውጤቱን የማግኘትና፣ በውጤቱ መሰረት ሌሎች ምርመራዎችን ማከናወንና ትንተና የማቅረብ፣ በርካታ ስራ የሚቀረውና ወንጀሉ ውስብስ በመሆኑ፣ ዜናው ከማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ መነሳቱ ሌሎችንም ማስረጃዎችንም ሊሰውሩ ስለሚችሉ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው አመልክቷል፡፡

በዚህም፣ ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁ “ምስክሮችን ሊያሸሹ ፣ ሊያስፈራሩ ፣ ሊደልሉ ስለሚችሉና ምርመራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ በመሆኑ” የ14 ቀናት ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

የጋዜጠኞቹ ጠበቃ በበኩሉ፣ በሽብር ፈጠራ ያስጠይቃቸዋል የተባለው ዜና፣ በፖሊስ እጅ የሚገኝ በመሆኑ ፣ ካስፈለገም የተሰራጨውን ዜና፣ ጣቢያው ለ30 ቀናት የማቆየት ሀላፊነት ስላለበት፣ በማንኛውም ጊዜ ማግኘት እንደሚቻል ማስረጃው ከድረ ገፁ ላይ የተነሳው በተቆጣጣሪው ባለስልጣን አስተያየት መሆኑን፣ በዋስ ቢለቀቁ የሚያሸሹት ማስረጃ እንደማይኖር ጠቅሶ፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር አመልክቷል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፣ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ የዋስ መብታቸውን የሚያስከለክል ባለመሆኑ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ብይን ሰጠ፡፡

በዚያኑ እለት፣ የዋስትና ፎርማሊቲ ተሟልቶ፣ ዳኛው የፈረሙበት ትዕዛዝ፣ ለወንጀል ምርመራው ቢሮ ደርሶታል፡፡ ግን እስረኞቹ አልተለቀቁም፡፡

መስከረም 8፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ይግባኝ ማለቱና ለመስከረም 12/2018 መቀጠሩ ተሰማ፡፡

መስከረም 12 ፣ ፌዴራል ፖሊስ ፣ ከመስከረም ሰባት ጀምሮ፣ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፣ በዘገባው ከድረ ገጹ ላይ መነሳቱ ፣ ለሌሎችንም ማስረጃዎች ሊያጠፉ እንደሚችሉ ስለሚያሳይ፣ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሻርለት ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት አመልክቷል፡፡

የጋዜጠኞቹ ጠበቃም፣ ደንበኞቹ የታሰሩት መስከረም 7 ሳይሆን ነሐሴ 28 ጀምሮ መሆኑን ፣ መረጃው ከድረ ገጹ ላይ የወረደው በተቆጣጣሪው ባለስልጣን አስተያየት መሆኑና ሙሉ ዜናው በፖሊስ እጅ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሶ ተከራክሩዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ነገሩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ መስከረም 14 ቀን 2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

ጋዜጠኞች ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በ ቁጥጥር ስር በዋሉ 21ኛው ቀን በተለዋጩ ቀጠሮ ቀን ፣ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የስር ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠው ውሳኔ አፅድቆ መዝገቡን ዘግቷል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…
https://n9.cl/2eejev