ትራምፕ የአሜሪካውን ዓለማቀፍ የልማትና ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) ሊዘጉት ነው

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካውን ዓለማቀፍ የልማትና ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት መስማማታቸውን ባለሃብቱ አማካሪያቸው ኤለን መስክ ዛሬ አስታውቋል።

መስክ፣ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ዕጣ ፋንታ ዙሪያ እንደተወያየና ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ እንደተወሰነ ገልጧል። መስክ፣ የልማት ድርጅቱ እንዲዘጋ የተወሰነው፣ ሊጠገን በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው በማለት ተናግሯል። መስክ፣ የልማት ድርጅቱ የወንጀል ድርጅት ኾኗል በማለትም ፈርጆታል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፣ የድርጅቱን አስተዳደራዊ ነጻነት በመግፈፍ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ሥር ለማዋቀር ስለማቀዱ ሰሞኑን ተዘግቦ ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ የምትሠጠው የውጭ ዕርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቋረጥ ባዘዙት መሠረት፣ ድርጅቱ እና ከድርጅቱ የዕርዳታ ገንዘብ የተቀበሉ አጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የዕርዳታ ሥራቸውን አቁመዋል።

የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ እስካኹን ተፈጻሚ ያልኾነባቸው የዕርዳታ መስኮች፣ የነፍስ አድን እና የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች ናቸው።