ስዊዘርላንድ ለኤርትራ ስትሠጠው የቆየችውን የቴክኒክ ድጋፍ ከቀጣዩ ግንቦት ወር ጀምሮ ለማቋረጥ መወሰኗን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ስዊዘርላንድ ላለፉት ስምንት ዓመታት ለኤርትራ የቴክኒክ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው፣ የአገሪቱ መንግሥት የዜጎቹን ስደት በመግታትና ስደተኞችን መልሶ በመቀበል ረገድ ተባባሪ እንዲኾን ለማበረታታት እንደነበር ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።
ኾኖም የስዊዘርላንድ መንግሥት በቅርቡ ባደረገው ግምገማ፣ ይህ ግብ እንዳልተሳካና የኤርትራ መንግሥት ስደተኞችን ለመቀበልም ኾነ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ተባባሪ እንዳልኾነ ማረጋገጡን ዘገባዎቹ ጨምረው አመልክተዋል።
ባሁኑ ወቅት 7 ሺሕ ያህል ኤርትራዊያን ስደተኞች ስዊዘርላንድ ውስጥ የተጠለሉ ሲኾን፣ 200ዎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተወስኖባቸዋል ተብሏል።
ስዊዘርላንድ ለኤርትራ በዋናነት የምትሠጠው ድጋፍ፣ ለወጣቶች የሙያ ሥልጠናዎችን መስጠት ነው።