(መሠረት ሚድያ)- ሁለት የሸገር ኤፍ ኤም ጋዜጠኞች ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሜክሲኮ ታስረው እንደሚገኙ በወቅቱ መረጃ ማቅረባችን ይታወሳል።
ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ በወቅቱ ከታሰረ ከሰዓታት በኋላ መለቀቁ የሚታወስ ሲሆን አርታኢዋ ትግስት ዘሪሁን እና ሪፖርተሯ ምንተአምር ፀጋው ግን አሁንም ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ማቆያ እንደሚገኙ ሚድያችን አረጋግጧል።

በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ቢፈቅድም ጋዜጠኞቹ እስካሁን አለመፈታታቸው ታውቋል።
ሸገር ኤፍ ኤም በበኩሉ በጉዳዩ ዙርያ ዝምታን የመረጠ ሲሆን በራሱ ጋዜጠኞች እስር ዙርያ የሰራውን የዜና ዘገባ ከገጾቹ አንስቷል።
“ትናንት ዋስትናቸው ከተፈቀደ በኋላ ይፈታሉ የሚል ተስፋ ነበረን፣ እስካሁኑ ሰዓት ግን ይህ አልሆነም” ያለው አንድ የመረጃ ምንጭ ሁለቱ ሴት ጋዜጠኞች በዓልን ጭምር በእስር ማሳለፋቸው ለቤተሰባቸው ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጉዳት አምጥቷል ብሏል።
“ተቋሙ እንኳን ድምፅ ሊሆናቸው አልቻለም፤ እንደታሰሩ መታሰራቸውን ከዘገበ በኋላ አጥፉ ተብለው ነው አሉ አጠፉት” በማለት አስተያየት የሰጠ አንድ የሙያ አጋራቸው ሁለቱም ታሳሪዎች ታታሪ ጋዜጠኞች መሆናቸውን ገልጿል።
“ሁለቱም ሴት ጋዜጠኞች ናቸው፣ ይሁንንና የሙያ ማህበራትም ሆኑ ሚዲያዎችም እንዲሁም የሴት መብት ተቆርቋሪዎችም ሁሉም ጉዳዩን እያነሱት እንኳን አይደለም። ማንም ድምፅ እየሆናቸው አይደለም” በማለት የተሰማውን ለሚድያችን አጋርቷል።
ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ ዙርያ ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረ ዜና ዙርያ መሆኑን የሚድያው ምንጮች ጠቁመው ዋና አዘጋጁ የተለቀቀው ዜናው ሲለቀቅ በስራ ላይ እንዳልነበር በመታወቁ ነው ብለዋል።
“ሸገር ኤፍኤም ለበርካታ አመታት እጅግ የበዙ ለመንግስት ግብዐትነት ጭምር ሆነው የሚያገለግሉ መረጃዎች ላይ ሲሰራ የነበረ ሚድያ ነው። ጥፋት እንኳን ተሰርቶ ከሆነ በብሮድካስት ህጉ መጠየቅ እየተቻለ ወደ እስር መሄዱ አሳዝኖኛል” በማለት አንድ ሌላ ባልደረባ ተናግረዋል።
-መሠረት ሚድያ-