በእስር ላይ ያሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ በጠና መታመማቸውን ቤተሰባቸው እና ጠበቃቸው ተናገሩ

በእስር ላይ የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ በጠና መታመማቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሰኞ ዕለት ታስረውበት ወደ ሚገኙበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሄደው እንደጎበኋቸው የገለጹት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ፣ አቶ ክርስቲያን በቅርቡ ቀዶ ሕክምና ከማድረጋቸው ጋር በተያያዘ ሕመማቸው እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የአቶ ክርስቲያን ታደለ አንድ ቤተሰብ አባልም፣አቶ ክርስቲያን ከወራት በፊት በመቅረዝ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን እና በቂ ክትትል ሳይደረግላቸው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲመለሱ መደረጋቸው አሁን ላሉበት ሁኔታ እንዳበቃቸው ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ በእስር ላይ እያሉ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት በእስር ላይ ይገኛሉ።

  • አቶ ክርስቲያን ታደለ

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአቶ ክርስቲያን የቤተሰብ አባል ለአቶ ክርስቲያን በሕክምናም ሆነ በፍርድ ቤት የተፈቀደላቸውን ለሕመማቸው ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን ማስገባት እንዳልተፈቀደላቸው እና ከአንድም ሁለቴ ምግብ መቅረብ ሳይችሉ መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ በሽብር ተከሰው ማረሚያ ቤት የሚገኙትን የምክር ቤት አባላት ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤቱ በሚያመሩበት ወቅት እንግልት እና መጉላላት ይደርስብናል ብለዋል።

አቶ ክርስቲያን ከወራት በፊት ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው እንደነበር ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው የገለጹ ሲሆን፣ በወቅቱ በተገቢው ሁኔታ ክትትል አግኝተው ሳያገግሙ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርገዋል ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ቅሬታ አሰምተው ነበር።

የአቶ ክርስቲያን ቤተሰቦች እንደሚሉት ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ ለመንቀሳቀስ እና ጠያቂዎችን ለማናገር አዳጋች በሆነ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በተጨማሪም “ወደ ማረሚያ ቤቱ ከተመለሰ በኋላም ለማገገም የሚያስፈልገው እንደ አጥሚት እና ሌሎች ነገሮችን ይዘን እንዳንገባ ተከልክለናል። ከአንድም ሁለት ጊዜ አጥሚት ይዘን ተመልሰናል። በጣም ነው የታመመው፤ በሥርዓት እንኳን ቆሞ አያናግረንም።”

የቤተሰቡ አባል የሆኑት ግለሰብ አቶ ክርስቲያን ሕክምና እንዲያገኙ እና ያሉበት ሁኔታ እንዲሻሻል የሰብዓዊ መብት አካላት “የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው ነው” ያሏቸውን እስረኞች እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ሌሎችም ግለሰቦች ላይ ክስ የመሠረተው ከአንድ ዓመት በፊት መጋቢት 2016 ዓ.ም. ነበር።

አቶ ክርስቲያን የወንጀል ሕጉን እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጣር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የተፈጸመ “ወንጀልን” እና የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በቀረበባቸው ክስ የዐቃቤ ሕግን ምስክሮችን ማሰማት የጀመረ ሲሆን፣ በመጪው ጥቅምት 10/ 2018 ዓ.ም. ጉዳያቸው መታየት ይቀጥላል።