የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ምናሴ ኃይሌ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል

ኢትዮጵያና አፍሪካ ታላቁን ልጃቸውን አጥተዋል!
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አገራቸውን ብሎም አሕጉራቸውን አፍሪካን በቅንነት፣ በታማኝነት፣ በአገር ፍቅር ስሜትና በልቀት ሲያገለገሉ የኖሩት ታላቁ የኢትዮጵያ አገልጋይ ዶክተር ምናሴ ኃይሌ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
ዶክተር ምናሴ ኃይሌ ከአባታቸው ከባላምባራስ ኃይሌ ድብነህ ከእናታቸው ወይዘሮ ኢሌኒ ኃይሌ ታኅሣሥ 24 ቀን 1922 ዓ.ም. ሐረር ከተማ የተወለዱት ሲሆን ከማንም በላይ የለፋላትን አገራቸውን ከኀምሳ አመታት በላይ ሳያዩ በስደት እንዳሉ በአሜሪካን አገር በኒውጀርሲ ጠቅላይ ግዛት ሕይዎታቸው አልፏል።
ከአለሙ ንጥል ብለው ከሚኖሩት ከእኒህ ታላቅ ሰው ጋር ስለዘመናቸው የመወያየት እድል ከገጠማቸው ሰዎች አንዱ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ስለ ሕይዎታቸው፣ ስለደከሙላት አገራቸውና ስለትዝብታቸው ያጫወቱኝ ብዙ ነው። ዶክተር ምናሴ ጨዋ፣ አገር ወዳድ፣ ሰው አክባሪና የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የደከመውን ድካም ከአረመኔዎቹ ከደርግና ወያኔ ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ያለማመንታት ሳይታክቱ ባሳተሟቸው ጥናታዊ ጽሑፎችና መጽሐፍት ታሪካችንን እንድናውቅ አድርገናል።
ዶክተር ምናሴ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ሕክምና በሚከታተሉበትም ወቅት ጤናቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ በስልክ በጠየቅኋቸው ወቅት ከነበሩን ቆይታዎቻችን መካከል ከታች የተያያዘው አጭር የስልክ ቆይታችን አንዱ ነው። ወደፊት በሌላ ጽሑፍ ሕይዎታቸውን እንዘክረዋለን!
በሰው ላይ ሞትን የሚያህል እዳ አለና ዶክተር ምናሴ ኃይሌ የማንም ባለጌ የሚፈነጭባትን የፉላትን አገራቸውን ሳያዩ ማለፋቸው እጅግ ያሳዝናል። እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው። ለወዳጆቻቸውና ለቤተሰባቸው በሙሉ ጽናትንና ብርታትን ፈጣሪ እንዲሰጣቸው ከልብ እመኛለሁ። የኢትዮጵያ አገልጋይ ሆነው ለአገርዎ ለከፈሉት መስዕዋትነትና ስለሰጡን ነገር ሁሉ እናመሰግንዎታለን! በሰላም ይረፉ!