የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የ”ሕወሓትን ህጋዊ ሠውነት መሻር ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አስታወቁ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሠ ወረደ የ”ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን ህጋዊ ሠውነት የመሻር ውሣኔ ተቀባይነት የለውም ብለው የገለፁ ሲሆን የፖለቲካ መፍትሔ እንዲሠጠውም” አሣስበዋል።
“ሕወሓት ሠርዤዋለሁ ተብሎ በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል ተራ ፓርቲ አይደለም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንጂ በቢሮክራሲያዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንደማይችል አፅንኦት ሠጥተዋል።
አብዛኛው የትግራይ ምሁራን፣ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ፣ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የገለጹ ሲሆን፣ ድርጅቱን “ታሪካዊ ፓርቲ” ሲሉ ጠርተው መሻሩ “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በምርጫ ቦርድ እና በሕወሓት መካከል ያለው አለመግባባት በድርድር መፈታት ያለበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ፓርቲው “ከምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት ቢቀበልም ድርድር ብቸኛው ዘላቂ መፍትሄ ነው” ሲሉም ለክልሉ ሚዲያዎች ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ ሕወሓት ደረጃውን ለማሟላት ቦርዱ ያዘዘውን “የማስተካከያ እርምጃዎች” በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድን ጨምሮ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት መሻሩ ይታወቃል።
በወቅቱ ሕወሓት ውሳኔውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ የፓርቲው ህጋዊነት የተረጋገጠው በፕሪቶሪያው የጦርነት ማቆም ስምምነት እንጂ በምርጫ ቦርድ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ማዕቀፍ እንዳልሆነ ተናግሯል። ፓርቲው እገዳውን ተከትሎ ከዚያ በኋላ የተሰጠውን ስረዛ “በህግ ደረጃ ትርጉም የለሽ” ሲል ቀደም ሲል ውድቅ አድርጎ ነበር።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ድርድር እንዲደረግ በማሳሰብ፣ የሕወሓት መሰረዝ የፕሪቶሪያን ስምምነት ሂደት አደጋ ላይ ሊጥል እና ሰፊውን የትግራይ የፖለቲካ ክፍል ሊያገለል እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። “የሕወሓት ከምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ጉዳይ በፖለቲካ መፈታት አለበት። ድርድር ብቸኛው መፍትሄ ነው” ብለዋል።
ይህ ውሳኔ ሕወሓትን እንደ “ህገወጥ የፖለቲካ ፓርቲ” ዳግም የሚመድበው ሲሆን፣ ይህም የምርጫ ቦርድ በጎርጎሮሳውያኑ ጥር 2021 የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት ለመሻር “በትጥቅ ትግል ውስጥ ተሳትፏል” በሚል የሰጠውን ውሳኔ እንደሚያድስ ተመላክቷል።