የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ በመንግስት ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ታወቀ

በፈረንሳይ ይገኛሉ የተባሉ ሁለት ጋዜጠኞች ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ በመንግስት ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ታወቀ
=================================
(መሠረት ሚድያ)- በቅርብ አመታት በርካታ ጋዜጠኞች ለደህንነታቸው በመስጋት በተለያየ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት ከሀገር መውጣታቸው ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ መንግስት በቅርብ ሳምንታት እና ወራት እነዚህ ጋዜጠኞች ከተቻለ ተላልፈው እንዲሰጡት፣ ካልሆነም ያሉበት ሀገራት መንግስታት ዝም እንዲያስብሏቸው እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ለመሠረት ሚድያ የደረሰ መረጃ ይጠቁማል።
ከነዚህ ጥረቶች መሀል በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ አፍሪካ እና በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የመንግስት ምንጮቻችን ተናግረዋል።
ከዚህ መሀል በፈረንሳይ ሀገር ይገኛሉ የተባሉ ሁለት የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ እንደነበር ታውቋል።
በመንግስት ስራ ዙርያ ተከታታይ መረጃዎችን በማውጣት እና የሰላ ትችት በመስጠት የሚታወቀው የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች ያየሰው ሽመልስ እና አበበ ባዩ የትኩረቱ ኢላማ እንደነበሩም ምንጫችን ተናግረዋል።
“ሁለቱ ጋዜጠኞች የሚሰሯቸው ዘገባዎች በመንግስት ዘንድ የራስ ምታት ሆነዋል፣ በዚህም ምክንያት በቅርቡ በጠ/ሚር አብይ አህመድ የተመራ የልዑክ ቡድን ፈረንሳይን በጎበኘበት ወቅት ሚድያው ትኩረት አግኝቶ ነበር” ያሉት እኚህ የመንግስት መረጃ ምንጫችን ናቸው።
በዚህ ግንቦት 14/2017 ዓ.ም በተደረገ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ወቅት ከተቻለ ሁለቱ ጋዜጠኞች ተላልፈው እንዲሰጡ፣ ካልሆነም ዝም እንዲሉ እንዲደረጉ በልዑክ ቡድኑ ለፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በቀጥታ ጥያቄ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ተቀባይነት እንዳጣ ታውቋል።
“ተላልፎ መስጠት የሚለው እንደማይሆን ቀድሞ የታሰበበት ይመስላል፣ ነገር ግን ጋዜጠኞቹን በዚህ ንግግር መሀል ስራቸውን ማስቆም እንዲቻል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። አልተሳካም” በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልፀዋል።
አክለውም “በመንግስት በኩል የቀረበው የማግባቢያ ሀሳብ ሁለቱ ጋዜጠኞች ፈረንሳይ ላይ ሆነው ካለ ስራ ፈቃድ ሀገራቸው ላይ እያሴሩ ስለሆነ ስራቸውን እንዲያቆሙ መጠየቅ ነበር። ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞቹ በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ መሀል ያለውን ግንኙነት እያበላሹ ነው፣ በምክንያትነት የተቀመጠው ደግሞ ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሟቸው ስምምነቶች ናቸው” በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
ኢትዮ ፎረም ዩትዩብ ላይ በየዕለቱ የሚያቀርባቸው ቪድዮዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካች የሚያገኙ ሲሆን አሁን ላይ ከ1.2 ሚልዮን በላይ ተከታታይ አለው።
መንግስት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በዩጋንዳ ያሉ ጋዜጠኞች ተይዘው እንዲሰጡት ለሀገሪቱ መንግስት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል።
መሠረት ሚድያ!