በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ እንደማይሳተፉ ለዋዜማ ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹ በሂደቱ ላለመሳተፍ የወሰኑት፣ ኮሚሽኑ ገልጽነትና ገለልተኝነት ይጎድለዋል፤ ክልሉም ከድኅረ-ጦርነት ቀውስ ገና አልወጣም በማለት ነው።
ሳልሳዊ ወያነ፣ የትግራይ ግዛቶች በሌሎች የታጠቁ አካላት እንደተያዙ መኾኑን ገልጦ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩም በሂደቱ ይሳተፋል ብሎ እንደማያምን አስታውቋል። ባይቶና እና አረና፣ አገራዊ ምክክሩ እስካኹን ባለው አካሄድ የአገሪቱን ችግር ይፈታል ብለው እንደማያምኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሳልሳዊ፣ አረናና ባይቶና፣ እስካኹን ከኮሚሽኑ የደረሳቸው የተሳትፎ ጥሪ እንደሌለ ጠቁመዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሂደቱ ይሳተፍ እንደኾን ዋዜማ ለማረጋገጥ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።