የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠረዉ አየር መንገድ የሞስኮ-ዋሽግተንና ብራስልሶች ጠብ ሰለባ እንዳይሆን በጥንቃቄ መጓዙን የመረጠ መስሏል።

አዲስ አበባ-የኢትዮጵያ አየር መንግድ ለሩሲያ አዉሮፕላን ማከራየት አይፈልግም-ዋና ሥራ አስፈፃሚ
DW : የኢትዮጵያ አየር መንግግድ ለሩሲያ አየር መንገዶች አዉሮፕላን ለማከራየት ተስማምቷል የሚለዉን ዘገባ አየር መንገዱ አስተባበለ።ዩክሬንን በመዉረሯ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ተባባሪዎቻቸዉ ተደጋጋሚ ማዕቀብ የጣሉባት የሩሲያ አየር መንገዶች አዉሮፕላንና የመለዋወጫ እጥረት ገጥሟቸዋል ይባላል።ችግሩን ለማቃለል ከኢትዮጵያና ከሌሎች ሐገራት አየር መንገዶች አዉሮፕላኖችን ለመከራየትና መለዋወጫዎችን ለመግዛት መስማማቷ ተዘግቧል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን (ግሩፕ) ዋና ሥራ አሥፈፃሚ መስፍን ጣሰዉ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ግን አየር መንገዳቸዉ አዉሮፕላኖቹን ለሩሲያ አየር መንገዶች ለማከራየት «ሐሳቡም የለዉም፤ ብንጠየቅም አናደርግዉም» ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሩሲያ አዉሮፕላን የማያከራይበት ምክንያት
የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደጠቀሰዉ አየር መንገዱ ለዉሳኔዉ ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት ዋና ሥራ አሥፈፃሚዉ አስታዉቀዋል።«አንደኛ እኛ ራሳችን አዉሮፕላን ተጨማሪ የምንፈልግበት እንጂ ለሌላ አካል የምናከራይበት ወቅት አይደለም።» አቶ መስፍን እንደ ሁለተኛ ምክንያት የጠቀሱት አየር መንገዳቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ አዉሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ አዉሮፕላን ሲገዛና በተለያዩ ሐገራት ሲበር የየሐገሩን ሕግ አክብሮ የሚሰራ መሆኑን ነዉ።«አሜሪካ ራሺያ ላይ ማዕቀብ እንደጣሉ እናዉቃለን፣ እኛ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር በጣም ብዙ ቁርኝት አለን።ሥለዚሕ የአሜሪካን ሕግ አክብረን ነዉ (የምንሰራዉ)፣ ያን ሕግ ካላከበርን የሚከተለዉን ችግር እንረዳለን።»
የሩሲያና የምዕራባዉያን ጠብ ያስከተለዉ ጣጣ
ኢትዮጵያ በተለይ በትምሕርት፣በሥልጠናና በጦር መሳሪያ ግዢ ከሩሲያ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት አላት።የሩሲያና የምዕራባዉያን መንግሥታት ጠብ ከናረ ወዲሕ ደግሞ BRICS በሚል ምሕፃረ ቃል በሚጠራዉ ምጣኔ ሐብታዊ ማሕበር አማካይነት ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ነዉ።የሩሲያ ሩብልንና የኢትዮጵያን ብር በቀጥታ መለዋወጥ ተጀምሯልም።ታዛቢዎች እንደሚገምቱት የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠረዉ አየር መንገድ የሞስኮ-ዋሽግተንና ብራስልሶች ጠብ ሰለባ እንዳይሆን በጥንቃቄ መጓዙን የመረጠ መስሏል።