በተመድ የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በቅርቡ ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ትብብርና ውህደት ያቀረቡትን ፍኖተ ካርታ “ቅንነት የጎደለው” እና “ኤርትራን ለኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ተገዢ ለማድረግ ያለመ ነው” በማለት አጣጥለውታል። አምባሳደር ሶፊያ፣ የዲና ሃተታ “በኤርትራ ትክሻ ላይ ኢትዮጵያ በውስጣዊና ቀጠናዊ ደረጃ የተበላሸባትን ምስል ለማደስ የተቀነባበረ ነው” ብለዋል። በሁለት ሉዓላዊ አገሮች መካከል ቀጠናዊ ትብብር ወይም ውህደት እንዲፈጠር የሚቀርብ ሃሳብ የቱንም ያህል ማራኪ ቢሆን፣ በመጀመሪያ መነሻውን “ታሪካዊ እውነታ” ላይ ማድረግ ይገባዋል- ብለዋል አምባሳደሯ። ድንበሮችና ሉዓላዊነት የማይገሠሱ መሆናቸው በማያሻማ ሁኔታ ሳይረጋገጥ፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጠናዊ ትብብር ለመመስረት የምትችልበት ሁኔታ እንደማይኖርም አምባሳደር ሶፊያ ገልጸዋል።