154 ኢትዮጵያውያንን ጭና መዳረሻዋን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ያደረገች ጀልባ በመስጠሟ አብዛኞቹ የራያ ልጆች ናቸው በአደጋው የሞቱት

” ወንድሜ ተርፏል መነሻው ከራያ ነው ሳምንት አልፏል ከቤት ከወጣ እና ከእሱ ጋር የነበሩት አብዛኛዎቹ ሞተዋል ” – ወንድም

🕯” ራያ አላማጣ አካባቢ ለሟች ቤተሰቦች መርዶ ተነግሯል ! ”

154 ኢትዮጵያውያንን ጭና መዳረሻዋን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ያደረገች ጀልባ በመስጠሟ እስካሁን የ68 ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፎ አስክሬናቸው ወዳድቆ መገኘቱ 12 ሰዎች በህይወት መትረፋቸው ሌሎቹ ግን የገቡበት እንደማይታወቅ አስክሬናቸውም እየተፈለገ እንደሆነ መነገሩ ይታወሳል።

በአሰቃቂው አደጋ ህይወታቸው ያለፉ ኢትዮጵያዊያን ወንድም እና እህቶቻችንን አስክሬን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተለቀቁ ይገኛል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአደጋው ወንድሙ በህይወት ከተረፈለት እና ወንድሙን በስልክ ማነጋገር የቻለን ሰው ከሳኡዲ አረቢያ አነጋግሯል።

ምን አለ ?

” እኔ ሳኡዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ ነው የምኖረው ወንድሜ ተነስቻለሁ ብሎ ከነገረኝ ሳምንት ይሞላዋል።

ከእሱ ጋር የአንድ አካባቢ ልጆች የሆኑ ጎረቤቶቻችን አብረው ተነስተዋል ከራያ መሆኒ አካባቢ።

ከእኛ ሰፈር ብቻ አራት ልጆች ሆነው ነው የተነሱት ከአላማጣ ደግሞ 3 ልጆች ተጨምረው በአጠቃላይ በአንድ ደላላ ሰባት ሆነው ወጥተዋል።

እንደ እድል ሆኖ የእኔ ወንድም እና አንድ ልጅ ተረፉ ከሞቱት ውስጥ ሁለቱ የአጎት ልጆች ናቸው ትላንት ማታ መርዶ ተነግሯቸዋል።

አብዛኞቹ የራያ ልጆች ናቸው በአደጋው የሞቱት።

ራያ አላማጣ አካባቢ ለሟች ቤተሰቦች መርዶ ተነግሯል።

ወንድሜ ሊደርሱ ትንሽ ሲቀራቸው ጀልባዋ መገልበጧን ነግሮኛል እጅግ ተደናግጦ ስለነበር ብዙ ነገር ሊነግረኝ አልቻለም።

በህገ ወጥ ጉዞ ላይ ጀልባ የሚያሽከረክሩ ደላላዎች የባህር ጠባቂዎችን ሲያዩ ይደናበራሉ ምናልባትም ይህ አደጋም የተፈጠረው የባህር ጠባቂዎችን ተመልክተው ሲደናገጡ ገልብጠዋቸው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ ” ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።