ፍልሰታ “እኛም ማየት አለብን” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
በየዓመቱ ከነሀሴ 1 እስከ 15 ድረስ የምትጾመው ፍልሰታን በዘልማድ ነው የምንጾማት ወይንስ ሚስጢሩን ተረድተነውና አውቀነው ነው ሲሉ ቀሲስ አስተርአየ ይጠይቃሉ። “የፍልሰታ ጾም ትንሿ የጤፍ እንደ ጤፏ ቅንጣት እየወደቅን እየተነሳን አድገን፥ እኛነታችንን ለሚቀጥለው ዘሮቻችን ለማቀበል በዚህ ምድር ላይ መዘራታችንን የምንመረምርበትየጥሞና ወቅታችን ናት። መንፈሳችን ከሥጋዊ ስሜትና ፍላጎት ርቆ ያጣነውን ፈልጎ ለማግኘት የሚሰማራበት ወቅት ናት”። ቀሲስ አስተርአየ በጽሁፋቸው አፅንዖት በመስጠት በብሔራዊና በመንፈሳዊ ስሜታቸው የተመኙትን አይተው ያለፉ ኢትዮጵያዊያን አርበኛ በላይ ዘለቀ፣ አቡነ ቴዎፍሎስንና ጋሼ አበራ በቀለን ከፍልሰታ ጾም መንፈስ ጋር ያላቸውን መስተጋብር በዝርዝር አስረድተዋል።
በተለይ ምዕመናንና ቤተ ክርስቲያንን በአውሬ አላስበላም ብለው እራሳቸውን መስዋዕት ስላደረጉላት አቡነ ቴዎፍሎስ ስናነሳ በአሁን ጊዜ ፓትርያርኩ፣ ሲኖዶሱና ጳጳሳቱ በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ፣ በስልጣን፣ በገንዘብ፣ በዝሙትና በተለያዩ ህጸጾች የተጨማለቁ መሆናቸውን ስንመለከት ምንኛ ያንገበግባል። ቤተክርስቲያኒቷና በአጠቃላይም አገሪቷ የወረዱበትን አዘቅትና መከራ እንዲሁም በአማራነታቸውና በተዋህዶ ዕምነት ተከታይነታቸው ብቻ በየዕለቱ ስለሚጨፈጨፉትና ሞታቸው ከዝንብ ሞት እኩል ስለተቆጠረባቸው ምዕመናን ስናጤን ጊዜው የምፅዓት ነው ወይ ያሰኛል። በሐዋርያት ስራ 20፡28 በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ እንደተጻፈልን “በገዛ ገንዘቡ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል በአሁን ጊዜ እንደተፈጸመብን አያጠራጥርም። በአቡነ ማቲያስ የሚመራው ሲኖዶስና ጳጳሳቱ በትክክል ነጣቂ ተኩላ መሆናቸውንና ለምዕመናን የማይጨነቁ ጨካኞች መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተውናል። የአሁኑ ይባስ እንደሚባለው በሽዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናንና ካህናት መጨፍጨፍ ምክንያት የሆኑትንና ምዕመናንን ማቅ ያስለበሱትን አቡነ ሳዊሮስን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርጎ የሾመ ሲኖዶስ የዲያብሎስ መገልገያ ተቋም ለመሆኑ ማስረጃ አያስፈልግም። በዝሙት ወንጀል ከአሜሪካ መንፈሳዊ ት/ቤት የተባረሩትን አቡነ ኤውስጣጢዎስን አባል አድርጎ የቀጠለ ሲኖዶስ ምን ያህል ከክርስትና ጋር የተጣረሰ የአብይ አህመድ መጫወጫ አሻንጉሊት መሆኑንን አገር ያወቀውና ፀሀይ የሞቀው ዕውነታ ነው።
እጅግ ጥልቅ መልዕክት ያዘለውንና ወቅታዊነት ያለውን በ16 ገጽ ተከሽኖ ከዋቢ መጽህት የተገኙ ወሳኝ ጥቅሶችን አካቶ የተዘጋጀውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። ፍልሰታ