በአስገዳጅ ሁኔታዎች ከሥራ ኃላፊነት መልቀቄን አስመልከቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!
እኔ ያሬድ ኃይለማርያም ከተመሰረተ አራት አመት ተኩል ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (Ethiopian Human Rights Defenders Center) በዋና ዳይሬከተርነት ሳገለግል ቆይቼ ባጋጠሙኝ አስገዳጅ ሁኔታዎች ከአገስት 1 ቀን 2025 (ሐምሌ 25 2017) ጀምሮ ከሃላፊነቴ እና ከድርጅቱ ለመልቀቅ መገደዴን ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
ይህ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋምና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ከሚገኙ አቻ ድርጅቶች ጎን ቆሞ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቶች መብት መከበርና አቅማቸውንም ለማጎልበት በርካታ ሥራዎችን እንዲሰራ ምሪት በመስጠትና በአጭር ጊዜም ውስጥ ድርጅቱ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭም እውቅና እና ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡
ድርጅቱ ከተመሰረተ አጭር እድሜ ያለው ቢሆንም ሲያከናውን የቆያቸው ሥራዎች እና አገሪቱ ውስጥ ለሚፈጽሙ የመብት ጥሰቶች፤ በተለይም በጋዜጠኞች፣ በሲቪል ማህበረሰብ አባላት እና በመብት ተሟጋቾ ላይ የሚፈጸሙ የመበት ጥሰቶችን በማጋለጥና መብታቸው እንዲከበርበአደባባይ በመሟገት ግንባር ቀደም ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ከድርጅቱ ጠንካራ ሠራተኞችና የቦርድ አባላት ጋርበመሆን ቁልፍ ሚና ስጫወት ቆይቻለሁ፡፡
ይሁንና ከአንድ አመት ወዲህ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚገኙ ሚዲያዎች ላይ እየቀረብኩ አገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የምሰጠቸው መገልጫዎችና ማብራሪያዎች፣ በማህበረ ድህረ ገጾች ላይ ዜጎችን ስለ መብታቸው እንዲያውቁና በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በማስመልከት የማካፍላቸው ሃሳቦችና የምሰነዝራቸው የሰሉ ትችቶች በአገዛዝ ሥርአቱ ዘንድ በጥሩ ሁኔታ እየታ ባለመምጣታቸው የተነሳ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አይነት ጫናዎችን ሳስተናግድ ቆይቻለሁ፡፡
የተለያዩ ዛቻዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ትንኮሳዎችን በጸጥታ አካላት በኩል ሲፈጸሙ እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ስልኮቼ ያልተለመዱ ጥሪዎችን ሳስተናግድ ያለውን ግልፅ ስጋት ችላ በማለት በሥራዬ ላይ አተኩሬ ቆይቻለሁ፡፡ ሆኖም በዚህ ሁኔታ ውስጥ በነጻነት ለመወጣትም ሆነ የተቀበልኩትን የሥራ ሃላፊነት በብቃት ለማከናወን የማልችልበት ደረጃ ላይ መድረሴን ስላረጋገጥኩ በተጓዳኝም በሥራ ጫና ብዛት ችላ ያልኳቸው የግል የጤና ጉዳዮችም ስለነበሩ እነዚህን ምክንያቶች በመጥቀስ ከወራቶች በፊት ለድርጅቱ ቦርድ የመልቀቂያ ጥያቄዬ አቅርቤ በምትኬ ሰው እንዲፈልጉ አሳውቄያለሁ፡፡
ቦርዱም ጥያቄዬን ተቀብሎ እስከ ዲሴምበር(ታህሳስ) ወር መጨረሻ 2025 ድረስ እንድቆይና አመራሩን የሚረከቡ ሠራተኞችን እያዘጋጀሁና እያሰለጠንኩ እንድቆይ ተስማምተን ነበር፡፡ ይሁንና ከላይ በገለጽኳቸው ምከንያቶች ከድርጅቱ ጋር የምቆይበት ጊዜ ከወራቶች ወደ ቀናት ለያጥር ችሏል፡፡ እኔም ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ከዛሬ ሁለት ሳምንት በፊት ለድርጅቱ ሌላ የመልቀቂያ ደብዳቤ ለማስገባት ተገድጃለሁ፡፡
ይሁንና እኔ ለድርጅቱ ቦርድ የመልቀቂያ ደብዳቤ ባስገባሁ በሳምንቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሐምሌ 14፣ 2017 በአንድ ከፍተኛ ሃላፊው በኩል ለሥራ ባልደረቦቼ ስልክ በመደወል ወደ ቢሯቸው ከጠሩ በኋላ እኔን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን ካነሱ በኋላ በግልጽ የድርጅቱ ቦርድ በአስቸኳይተሰብስቦ እኔን ከምመራው ድርጅት ሃላፊነት ጋር ተያይዞ ያላቸውን አቋምና ውሳኔን በደብዳቤ ለባለሥልጣን መሥሪያቤቱ በጽሑፍ እንዲያሳውቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን እኔ ቀደም ብዮ በራሴ ፍቃድ ሁኔታዎችን ከመረመርኩ በኋላ ከሥራ የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገባሁ ቢሆንም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግን ፍጹም አግባብነት በሌለው መልኩ በድርጅቱ የውስጥ አሰራር ጣልቃ የገባ ተግባር ፈጽሟል፡፡
የዚህም ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና አላማዎች፤
1ኛ/ ይህ መግለጫ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በማናቸውም ሚዲያ ልቀርብና ሃሳቤንም ላካፍል የምችለው እራሴን በመወከልና እንደ አንድ የሰብአዊ መብት ባለሙያ እንጂ እስከ አሁን ስመራ የቆየሁትንም ሆነ የትኛውንም ድርጅት ወክዬ እንዳልሆነ ለማሳወቅ ነው፡፡ በማህበራዊ ድህረ ገጾችም ከዚህ በኋላ የማካፍላቸው መረጃዎች እና የማስተላልፋቸው መልዕከቶች እኔን ብቻ የሚወከሉ እና እንደ አንድ በግል ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንደሚቆረቆር ተሟጋች መሆኑን ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች፤ በተለይም በየጊዜው በመድረካቸው ሃሳቤን እንዳቀርብ ለሚያስተናግዱኝ መገናኛ ብዘሃን ለማሳወቅ ነው::
2ኛ/ ሁለተኛውና እጅግ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው የምፈልገው ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ መሻሻሎች ታይተወብት የነበረው የአገራችን የሲቪከ ምህዳር ዳግም እየተዘጋና ከፍተኛ አደጋዎችም ከፊቱ የተደቀኑ መሆኑን እና ሚዲያዎችም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥተው መንግስት በሲቪል ማህበራት ላይ እና በምህዳሩ ላይ እያሳደረ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጫና ትኩረት ሰጥታቸው እውነታውን ለህዝብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቃችውን ተግታችሁ እንድትቀጥሉ ለማሳሰብ ነው፡፡ መንግስት የሲቪክ ምህዳሩን መልሶ በከፋ ጫና ውስጥ ለማቆየት እያረቀቀ ያለውን እጅግ አደገኛ የህግ ማሻሻያ ጨምሮ በሲቪል ማህበራት ላይ ውስጥ ለውስጥ እያደረሰ ላለው ጫና ከላይ የጠቀስኩት በእኔ እና በሌሎች አገር ጥለው እንዲሰደዱ በተደረጉት የኢሰመጉ የቀድሞ ዋና ዳይሬከተር አቶ ዳን ይርጋ ሌሎችም ተቋማት ጉዳይ በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡
3ኛ/ ላለፉት ስድስት ወራት ያህል በማህበራዊ ድህረ ገጾች በተለይም በፌስቡክና በቴሌግራም ዘወትር ቅዳሜ “መልዕከተ ቅዳሜ” በሚል ከአንድ አመት በላይ ያለምንም ማሰለስ ማህበረሰባችንን ስለ መብቱ እንዲያውቅና በአንዳንድ ወሳኝ በሆኑ የመብት ነክ ጉዳዮች ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ ውይይት አጫሪ የሆኑ አጫጭር መጣጥፎችን ከማካፈል ተቆጥቤ ቆይቻለሁ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ስመራው በቆየሁት ድርጅት ላይ ለደርሱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ በሚል ነበር፡፡ እኔ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ በቋሚነት በመምጣት ሰፋፉና ጥልቅ ቁምነገሮች ላይ በማተኮር የግል ምልከታዬን ለማካፈል የወሰንኩት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሚዲያ ምህዳር እጅግ እየጠበበና በተለይም የሰላ ትችት በመሰንዘርየሚታወቁ የህትመት ጋዜጣዎችና መጽሄቶች በመንግስት በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና እና ወከባ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በመቋረጣቸው ማህበረሰባችን ትምህርት ሊያገኝባቸው የሚችሉ መድረኮች ጠበዋል ከሚል መነሻ ነው:: በመሆኑም ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ በቋሚነት በሙሉም የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በሰብአዊ መብት እና ተያያዥ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በቋሚነት ትንታኔዎችን እና የግል ምልከታዎቼን የማካፍል መሆኑን እየገለጽኩ የተለመደው መረጃዎችን የማጋራት ትብብራችሁ እንዳይለየኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ ወይም ማብራሪያ ለምትፈልጉ የሚዲያ ባለሙያዎች በማናቸውም ጊዜ በቀጥታ ልታገኙን እንደምትችሉ እየገለጽኩ እስከ ዛሬ መድረኮቻችሁን ከፍት በማድረኛ ለሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት በቃለ ምልልስ፣ ጽሁፎቼን በማጋራት ወይም በማናቸውም መልኩ መድረክላመቻቻችሁልኝ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ሁሉ ምስጋናዮ የላቀ ነው፡፡
አሁንም ለተገፉ እና መብታቸው ለተጣሰባቸው ሰዎች ሁሉ ድምጽ የመሆን ቁርጠኝነቱ ከእኔ ጋር ስለሆነ በማናቸው ጊዜ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ለምታደርጉት ጥረት እና ለምትፈልጉት መረጃና ማብራሪያ ሁሉ የበኩሌን ቀና ትብብርና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን በታላቅ ትህትና እገልጻለሁ፡፡
ያሬድ ኃይለማርያም
በሰብአዊ መብቶች አማካሪና ተመራማሪ