“ጦርነት ያብቃ፣ ሠላምና ዲሞክራሲ ይስፈን” የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓረቲዎች ኮክሰ

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ኹኔታ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን “ተስፋ ሰጪ ነገሮች የማይታዩበት” ነው ሲል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓረቲዎቸ ስብስብ – ኮክሰ ሥጋቱን ገለፀ። በቅድሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የአሰራርና ተቋማዊ” ያላቸው ችግሮች እንዲፈቱ የጠየቀው ኮከስ በተቋሙ “እውነተኛ ሪፎርም ከሌለ ተዓማኒ፣ አካታች፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊኖር አይቸልም” ብሏል። በዋናነት 8 የፓለቲካ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ ያደርጉበታል የተባለው ኮከስ ስለ ምርጫ ከመታሰቡ በፊት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ጦርነት እና ግጭቶች እንዲቆሙ፣ ሰላም እንዲሰፍን እና በተለይ ከኤርትራ ጋር እየተስተዋለ ያለው ውጥረት እንዲፈታ ጠይቋል።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓረቲዎቸ ስብስብ – ኮክሰ ዛሬ ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭጦች እንዲቆሙ ደጋግሞ ቢጠይቅም አሁንም ለሀገር ደኅንነት ሥጋት ሆነው መቀጠላቸውን ገልጿል። የዚህ ስብስብ አባል ፓርቲ የሆነው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ “ጦርነት ይብቃ” የሚለው አሁንም ዋና የጥሪያቸው ጭብጥ መሆኑን ገልፀዋል።

“ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ ከተፈለገ ጦርነት መቆም አለበት። ይሄ ነገር እየሰፋ በሄደ ቁጥር ይቺ ሀገር እያየን ልትፈርስ ትችላለች”።

ኮከስ ቀጣዩን ምርጫ ለማከናወን አስቻይ ኹኔታ የለም ብሏል

ኮከስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጅምሩ “የነጻነት እና የገለልተኝነት” ጥያቄዎች እንደሚነሱበት በመጥቀስ አሁንም አሉበት ያላቸው “የአሰራርና ተቋማዊ ችግሮች” እስካልተፈቱ ድረስ “ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ሊኖር አይችልም” ብሏል፡፡ “እውነተኛ ሪፎርም ከሌለ ተዓማኒ፣ አካታች፣ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ”  ሊኖር እንደማይችልም አቋሙን ይፋ አድርጓል።

“ሕዝብ ሰላማዊ ባልሆነበት ኹኔታ ዲሞክራሲን አይደለም የሚመርጠው። ሕዝብ ፍርሃት ውስጥ አስገብቶ የሚደረግ ምርጭ ተቃዋሚን የመመረጥ ፍላጎት አይኖረውም።….አሁን ባለው ኹኔታ ብዙም ተስፋ ሰጪ ነገሮች አይታዩም [ምርጫ ለማካሄድ]።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሕዝብን አመኔታ እንዲያገኝ በሁሉም ፓርቲዎች ሙሉ ስምምነት ላይ ተመስርቶ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር” ባለፈው ሳምንት በኦፌኮ ለቀረበበት ተመሳሳይ ጥያቄ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ ይህ ጥያቄ ቦርዱን ላዋቀረው አካል የሚቀርብ መሆኑን ጠቅሰው “ቦርድ ላለፉት ስድስት ዓመታት በገለልተኝነት ሲሠራ እንደነበረው አሁንም በገለልተኝነት እየሠራ ያለ ተቋም ነው”። ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር ።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስላለዉ ዉጥረት 

ኮከስ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የተገባው “እሰጥ አገባ በእጀጉ ያስፈራል” ሲልም ውጥረቱ ወደ ግጭት አምርቶ ቀጣናዊ ቀዉስ ከማስከተሉ በፊት መንግሥት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲከተል አሳስቧል። ላቀረበው ጥሪም “ከሐቀኛ ብሔራዊ መግባባትና ድርድር የሚመነጭ መፍትሔ” እንዲዘጋጅ ጠይቋል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ -ኮከስ በገዢው ፓርቲ እና መንግሥት ላይ ለሚያደርገው ጫና ሕዝብ ከጎኑ እንዲቆም ጠይቋል።

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በሀገራዊ ሰላም ጉዳይ ቢሾፍቱ ውስጥ ውይይት ያደረጉ ከ50 በላይ ፓርቲዎች “በሀገራችን ላይ ያለው አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” በማለት “መንግሥት በትጥቅ ግጭት ውስጥ ካሉ ኃይላት ጋር ወደ ድርድር እንዲገባ” ተጠይቋል።