መቀጣጫው ለእኔ ሳይሆን ለእናንተ ነው! ( ልደቱ አያሌው )
በቅርቡ- “መኖሪያ ቤትህን በ10 ቀን ውስጥ የማህበረሰብ ፖሊስ ጣቢያ ላደርገው ነው” ብሎ የዛተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አገዛዝ ዛቻውን ለመፈጸም 10 ቀንም መታገስ አልቻለም።
ከሁለት ቀን በፊት ያለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ የቤተሰቤ ንብረት የሆነውን መኖሪያ ቤቴን ከነ ሙሉ እቃው በመቀማት (መውረስ አይደለም) ፖሊሶች ገብተውበታል። ቀደም ሲል እንዳሉት የማህበረሰብ ፖሊስ ጣቢያ ያድርጉት
ወይም የባለስልጣን መኖሪያ እስካሁን በግልፅ አላዎቅነም። ይህንን ማድረግ አልበቃቸው ብሎም የቤቴን ጠባቂ
ያለምንም ምክኒያት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስረውታል።
ይህ አገዛዝ አይፈጽመውም ብዬ የምገምተው ምንም ዓይነት ነውርና ወንጀል ባይኖርም፣ ይህ የጠቅላይ
ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዐይን ያዎጣ የወንጀል ድርጊት የፖለቲካ አንደምታው ምን እንደሆነ እይታየን
ለህዝብ ማካፈል ስለፈለግሁ ይህችን አጭር መጣጥፍ ላስነብባችሁ ወደድኩ።
በኢትዮዽያ ፖለቲካ ተሳታፊ ከሆንኩ 33 ዓመት ሆኖኛል። በ27 ዓመቱ የኢህአዴግ አገዛዝ 5 ጊዜ ታስሬ ተፈትቻለሁ። ለ18 ቀናት የቤትና የቢሮ ውስጥ እገታ፣ ለ120 ተከታታይ ቀናት የደህንነት ክትትልና ማዋከብ፣ቢያንስ ለ20 ተከታታይ ዓመታት የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶብኛል።
አጸያፊ ስድብና መለስተኛ ድብደባ የደረሰብኝ ወቅትም ነበር። በእነዚህ ሁሉ ተጽዕኖዎች ምክኒያት ለተለያዩ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የጤና ችግሮች ተጋላጭ ሆኛለሁ።
ይህ ሁሉ በደል ሲደርስብኝ ግን በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረው የኢህአዴግ አገዛዝ በእኔ ላይ ለሚፈጽማቸው
ህገ-ወጥ ድርጊቶች ቢያንስ ህጋዊ ሽፋን ለመስጠትና ለማስመሰል በተቻለው አቅም ይሞክር ነበር። በእኔ
የፖለቲካ ተሳትፎ ምክኒያትም በቤተሰቦቸና በጓደኞቸ ላይ አንድም ጊዜ ችግር ለመፍጠርና የግል ንብረቴን ለመውረስ ሞክሮ አያውቅም።
አባል የነበርኩበትን ፓርቲም ለመከፋፈልና ለማዳከም እንጂ ህጋዊ እውቅናውን ለመሰረዝ ደፍሮ አያውቅም።
የ27 ዓመቱ አገዝዝ ይህንን ሁሉ አድርጐ እንዳሰበው እኔን ተስፋ ሊያስቆርጠኝና ከትግሉ ሜዳ ሊያርቀኝ አልቻለም።
ይልቁንም ግብዙና የእኛን ምክረ-ሀሳብ ለመቀበል የተሳነው የኢህአዴግ አገዛዝ በገጠመው ውስጣዊ የመዳከምና የመበስበስ ችግር ምክኒያት እራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የህልውና አደጋ አጋለጠ።
የዚያው የ27 ዓመቱ ስርዓት ቅሪት አካል የሆነው የወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ ለስልጣን ከበቃ
በኋላም የባሰና የከፋ እንጅ የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። የወቅቱ አገዛዝ እንኳንስ ፍትሀዊና ሀቀኛ
መሆን መቻል፣ ቢያንስ እንደ 27 ዓመቱ የኢህአዴግ አገዛዝ ለሚፈጽማቸው ወንጀሎች ህጋዊ ሽፋን ለመስጠትና ለማስመሰል የሚያስችል ብቃትም ሆነ ፍላጐት ሊኖረው አልቻለም።
የወቅቱ አገዛዝ ለ22 ዓመት በትግል ላይ የነበረውንና ለብዙ አዎንታዊ ለውጦች ፋና-ወጊ የነበረውን ኢዴፓን
በፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋና በወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ትብብር ህጋዊ እውቅናውን እንዲያጣ አድርጐታል።
ያለምንም ህጋዊ ምክኒያት በሶስት የፈጠራ ክስ በኦሮሚያ ክልል አስሮ ለአምስት ወራት አሰቃይቶኛል። በተከሰስኩባቸው በሁሉም ክሶች ፍርድ ቤት “ነፃ ነህ” ብሎ ቢፈርድልኝም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሶስት ጊዜ
በመጣስ በጉልበት በእስር ቤት አቆይቶኛል። ከብዙ ውጣ-ውረድ በኋላ ከእስር ቤት መውጣት ብችልም ወደ
ውጭ ሀገር ሂጀ እንዳልታከም በመከልከል ለሶስት ወራት ያህል አጉላልቶኛል።
በውጭ ሀገር በህክምና ላይ ባለሁበት ወቅትም ያለምንም ተጨባጭ መረጃ በሰላማዊ ትግል ጠበቃነቴ የምታዎቀውን ሰው በሽብርተኛነት በመወንጀል በኢንተር-ፖል ጭምር ሊያሲይዘኝ እያስፈለገኝ እንደሆነ አድርጐ የሀሰት ቅስቀሳ አካሂዶብኛል።
ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ ሳይመሰረትብኝም በስሜ ተመዝግቦ የሚገኝ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቴ ላይ እገዳ እንዲጣል አድርጓል።
ህክምናየን ጨርሸና በህግ የሚያስጠይቀኝ ጉዳይም ካለ ተጠያቂ ለመሆን ወስኘ ወደ ሀገሬ ለመመለስ ስሞክርም ከሀገሬ እንዳልዎጣ በመከልከል ሲያጉላላኝ የነበረውና “በወንጀል እፈልገዋለሁ” ሲለኝ የነበረው
አገዛዝ እንደገና ያለምንም ህጋዊ መሰረት ወደ ሀገሬ ተመልሸ እንዳልገባ ከለከለኝ።
ይህንን ካደረገ በኋላም የእኔን፣ የቤተሰቦቸን እና የጓደኞቸን የጋራ ንብረት ያለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ መውረስ ጀመረ።
“በሽብርተኛነት ወንጀል የተከሰሱና ንብረታቸው የሚዎረስ ዜጐች በአካል ቀርበው ካልሆነ በስተቀር በወኪልም ሆነ በጠበቃ መከራከር አይችሉም” የሚል የዘረፋ ህግ ሆን ብሎና አስቀድሞ አውጥቶ ስለነበር ወደ
ሀገሬ ሂጀ በፍትህ አደባባይ ለመዳኘት ያለኝን መብትም አሳጣኝ።
በወቅቱ አገዛዝ ከደረሰብኝ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ የእኔ፣ የጓደኞቸና የቤተሰቦቸ ንብረት የሆነና በመቅቱ የጋሸበ የገበያ ዋጋ ግምቱ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረታችን በህገ-ወጥ መንገድ በአገዛዙ ተዘርፏል። ይህ ዛሬ በእኔ ላይ የተጀመረው የዝርፊያ እርምጃም በእኔ ላይ የሚቆም ሳይሆን
ነገ ከነገ ወዲያ ለእራሳችሁ፣ ለልጆቻችሁና ለሀገራችሁ መብትና ጥቅም ተቆርቋሪ በመሆን አገዛዙን ለመታገል
ለምትሞክሩ ዜጐች ሁሉ በየተራ የሚዳረስ ድርጊት ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም።
የአገዛዙ ጥቃት የተሰነዘረው በእኔ በግለሰቡ “ልደቱ” ላይ ሳይሆን ስለ መብቱ መከበር ለመታገል በሚሞክር
በማንኛውም ዜጋ ላይ ነው። የኢህአዴግም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገዛዝ በእኔ ላይ ይህንን ሁሉ በደል
የፈጸሙበት ምክኒያት ከእኔ ጋር የተለዬ የግል ጠብና ጥላቻ ስላላቸው አይደለም። ምክኒያታቸው ሌላ ሳይሆን
ለሰላማዊ ትግል ያላቸው ስጋትና ፍርሃት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ነው።
የኢትዮዽያ ህዝብ አንድ ቀን እኔና እኔን መሰል ሰዎች የምናቀነቅነውን የሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኛነት ትግልን ሀያልነት በውል ተገንዝቦ ሆ… ብሎ ከተነሳ ህልውናው በአጭር ጊዜ እንደሚያከትም አገዛዙ ከማንም በላይ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ነው።
በፖለቲካ አመለካከቴ ምክኒያት ወደምወዳትና እንድትለዎጥ ብዙ ዋጋ ወደ ከፈልኩባት ሀገሬ እንዳልገባ መከልከሌም ሆነ ዕድሜ ልኬን ያፈራሁትን ሀብትና ንብረት ተነጥቄ በአንድ ጊዜ የነተበ ድሀ እንድሆን መደረጌ አገዛዙን ልታገለው መወሰኔ ምን ያህል ተገቢና ምክኒያታዊ መሆኑን የበለጠ አረጋግጦልኛል። ነገር ግን ትግሉ ውድና ብቸኛ ህይዎቴን ጭምር ለመስጠት ወስኘ የገባሁበት ስለሆነ ይህ ዓይነቱ ግፍ ለምን በእኔ ላይ ደረሰ ብዬ ልደነቅና ላማርር አልችልም።
እንደ አንድ የትግል ሰው የሆነውን ሁሉ ከነህመሙ በፀጋ ተቀብየዋለሁ።
ምክኒያቱም አገዛዙ በህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጭምር እንደ ቋሚ ስራው እየፈጸመ በሚገኝበትና
እራሱ የሀገሪቱ ህልውናም ከመኖር ወደ አለመኖር እየተቀየረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለእኔ ዓይነቱ የትግል ሰው
ሀብትና ንብረትን ማጣት የማይጠበቅ ድርጊት አይደለም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስልጣን ላይ እስከቀጠሉ ድረስ አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ በሂደት ሀብትና ንብረቱን ብቻ ሳይሆን ውድ ህይዎቱንና ሀገሩን ጭምር ማጣቱ አይቀርም የሚል ከተጨባጭ ግምገማ የመነጨ ግምት ስላለኝ ዛሬ በእኔ ላይ የተፈጸመው የቅሚያ ወንጀል እምብዛም አያስደንቀኝም። በህዝብ እልቂት ጭምር
የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም የሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ለእኔ ለስልጣን ተቀናቃኙ ለሆንኩት ሰው ቅንጣት
ያህል ርህራሄ እንዲኖረው አልጠብቅም።
ነገር ግን በእኔ ምክኒያት ያለአበሳቸው ጓደኞቸና ቤተሰቦቸ ንብረታቸውን በግፍ ሲነጠቁ ማየቴ ምን ያህል
ስሜቴን እንደረበሸውና እንደጐዳው መደበቅ አልችልም። ይህንን እውነታ ማንኛውም ህሊና ያለው ዜጋ
እራሱን በእኔ ቦታ ላይ አስቀምጦ ለመረዳት ቢሞክር ክብደቱን በቀላሉ ይገነዘበዋል ብዬ እገምታለሁ።
ስለሆነም ትንሽ የፍትህ እንጥፍጣፊ በልቡ ውስጥ ያለው ማንኛውም ዜጋ ቢያንስ የተፈጸመብኝን በደል
ባልተገባ ሰበብ አስባብ ለማስተባበልና ለማድበስበስ ሳይሞክር ስሜቴን በመጋራትና የደረሰብኝን ግፍና በደል
በማውገዝ የሞራል እገዛ ያደርግልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ይህንን የህሊና ፍርድ ጥያቄ የማቀርበውም አገዛዙን ለሚቃዎመው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ ውስጥና
ዙሪያ ለምትገኙና በማዎቅም ይሁን ባለማዎቅ “
መንግስታችን ፍትሃዊ ነው” በማለት ለመመፃደቅ
ለምትሞክሩ ዜጐች ጭምር ነው። ከእኔ ጋር የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራችሁ “የሰው ልጅ”
መሆንን በመጋራታችን ብቻ ይህንን በእኔ ላይ የተፈፀመ ዓይን ያዎጣ ወንጀል ልታዎግዙት ይገባል ብዬ
አምናለሁ።
በእኔ በኩል ሌላ የማድረግ አቅም ባይኖረኝም በእኔ ምክኒያት ያለ አበሳችሁ ንብረታችሁን በግፍ ለተነጠቃችሁ
ጓደኞቸና ቤተሰቦቸ ተጠያቂነቱ የእኔ ነውና ቢያንስ በዚህ አጋጣሚ በህዝብ ፊት ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
የደረሰባችሁን በደልና ኪሳራ ወደፊት ጊዜ፣ ፍትህና ፈጣሪ እንዲክሳችሁ እመኛለሁ።
ይህ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ እንኳንስ የአንድ ጥሩ መንግስትን የክፉ አምባገናዊ አገዛዝን
መመዘኛም የሚያሟላ አይደለም። እንዲህ ያለ ክፉና ስርዓት አልበኛ አገዛዝ ሀገራችን በቅርብም ሆነ በሩቅ
ጊዜ ታሪኳ አጋጥሟት አያውቅም። ይህ አገዛዝ በሰዎች ስብስብ ከተፈጠረ መጥፎ አገዛዝም በላይ ከአንድ
ክፉ፣ ጨካኝና ተንኮለኛ ግለሰብ ጋር እንኳን የሚመጣጠን ስብዕና የለውም።
“በሽበርተኝነት ወንጀል እያስፈለግሁት ነው” ያለውን ዜጋ ወደ ሀገሩ እንዳይገባ የሚከለክል፣ ከከለከለም በኋላ ንብረቱን ቀምቶ በጠበቃም ሆነ በወኪል መከራከር አትችልም የሚል ቅጥ-የለሽ ቀማኛ መንግስት በዓለምም ሆነ በሀገራችን
ታሪክ ታይቶ አያውቅም።
ይህ አገዛዝ በህዝብ ትግል ተሸንፎ ስልጣኑን እስካላጣ ድረስም እንኳንስ ሀብት ንብረታችን፣ እንኳንስ ግላዊ መብታችንና ህይዎታችን ህዝባዊና ሀገራዊ ህልውናችንም ከጥፋት ሊድን አይችልም።
አገዛዙ ከእኔም አልፎ በጓደኞቸና በቤተሰቦቸ ላይ በዚህ መጠን መዝመት የጀመረው ይህንን በማድረግ “ልደቱን
ከፖለቲካ እንዲርቅ አደርገዋለሁ” ብሎ በማሰቡ አይደለም። አገዛዙ እኔን በማንኛውም ተጽዕኖና አፈና ከትግሉ ውጭ ማድረግ እንደማይችል ከማንም በላይ ጠንቅቆ ያውቃል። ይልቁንም የአገዛዙ ዋና ዓላማ ሌሎች ዜጐች እኔን በመቀጣጫነት አይተው በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዲቆርጡና የፖለቲካ ትግሉ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው።
ይህንን በማድረግም “ሰላማዊ ትግሉ አይሰራም” የሚለውን የተሳሳተና አገዛዙን የሚጠቅም የአንዳንድ ወገኖች አመለካከት የበለጠ ማጠናከር መቻል ነው።
በአጭሩ የአረመኔው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሴራ እኔን ማስፈራራት ሳይሆን በእኔ መቀጣጫነት
እናንተን በፍርሃት አሸማቆ ለመግዛት መሞከር ነው። ይህንን የአገዛዙን የመቀጣጫነት ሴራ በብቃት ልናከሽፈው የምንችለው እሱ እንዳቀደው በመፍራትና ከትግሉ ሜዳ በመሸሽ አይደለም።
በመፍራትና በመሸሽ ልናፋጥነውና አይቀሬ ልናደርገው እንጂ ከቶውንም ልናስቀረው የምንችል ምንም ዓይነት አደጋ
የለም። የሚያዋጣን በእልህና በቁጭት የሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኛነት ትግልን በሀገሪቱ በማቀጣጠል አገዛዙ
እንኳንስ ንብረት በመቀማት በመግደልም ጭምር ሊያሸንፈን እንደማይችል በተግባር በማሳየትና እራሱ
ተስፋውን እንዲቆርጥ በማድረግ ብቻ ነው።
ልደቱ አያሌው
ሀምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም