በማስተርስ ዲግሪ ተመርቃ ጉሊት የምትቸረችረው የደምቢዶሎዋ መምህርት

አባይነሽ ሐምቢሳ

በደምቢዶሎ ከተማ በሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ተመርቃ መንገድ ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ በመቸርቸር የምትተዳደረው መምህርት ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርቶ በርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል።

አባይነሽ ሐምቢሳ የተባለችው ይህች መምህርት ከደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ በሒሳብ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪዋን ያገኘችው በማዕረግ ነው።

ይህች መምህርት ላለፉት ዓመታት ትምህርት በሚዘጋበት በክረምት ወቅት እንዲሁም በእረፍት ቀኗ ቅዳሜዎችን መንገድ ላይ በመቸርቸር ነው ኑሮዋን የምትደግፈው።

ለ13 ዓመታት በመምህርነት ያገለገለችው አባይነሽ በየወሩ የምታገኛት 7,500 ብር ደመወዝ ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ኑሮዋን መደጎም ስላዳገታት ነው ወደ ጉሊት የወጣችው።

“የማገኘው ደሞዝ ልጆቼን ለማስተዳደር፣ ማኅበራዊ ሕይወቴን ለመደገፍ፣ ለትምህርት፤ ለአጠቃላይ ለኑሮዬ በቂ አይደለም። በአሁኑ ሰዓት ለመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ በቂ አይደለም፤ ያለውን የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ አይደለም” ትላለች።

ከማስተማር ሥራዋ ጎን ለጎን ትምህርቷን በከፍተኛ ደረጃ መቀጠሉ አስፈላጊ ሆና ያገኘችው አባይነሽ፣ የማስተርስ ትምህርቷን ለመደጎምም ሌላኛው አማራጩ ጉሊት ነበር።

“በወር ደሞዜ የትምህርቴን ከፍዬ፣ ኑሮዬን ደግፌ፣ ለልጆቼ አውጥቼ አይሆንም” ስትል የአራት ልጆች እናት የሆነችው አባይነሽ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ገልጻለች።

በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ዩብዶ ወረዳ የተወለደችው አባይነሽ የጉሊት ችርቻሮዋን የጀመረችው ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።

ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ እና አቮካዶ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ከደምቢዶሎ ከ20 አስከ 25 ደቂቃ በእግር የሚያስኬድ መንገድ ከሚጠይቀው ስፍራ ተሸክማ አምጥታ በከተማዋ ትችረችራለች።

ገበያ በደራበትም ቀንም ከ200 አስከ 500 ብር ታገኛለች።

“ከማገኘው ትርፍ 100 ወይም 200 ብር አስቀምጬ ቀሪውን ደግሞ ለቤተሰቤ የሚያስፈልጉ እንደ ሳሙና፣ ስኳር ወይም ሌሎች ነገሮችን እገዛለሁ” ትላለች።

ሌላው ደግሞ ለትምህርት ቤት ክፍያዋ ይውል ነበር።

አባይነሽ ሐምቢሳ

 

“ይህንን የጉሊት ንግድ የጀመርኩት የሦስት ወር ልጆቼን ቤቴ ትቼ ነው” የምትለው አባይነሽ፣ ከጉሊት የምታገኘውን ገንዘብ ለልጆቿ ወተት እና ሌሎች የቤት ሸቀጦች በመግዛት ኑሮዋን መደጎሟን ታስረዳለች።

አባይነሽ እንደምትለው የጉሊት ችርቻሮዋን ከጀመረች በኋላ በተወሰነ መልኩ ኑሯቸው ተሻሽሏል።

አባይነሽ የደምቢደሎ መምህራን ኮሌጅን የተቀላቀለችው በ2001 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በኋላ በሂሳብ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቃለች።

በቄለም ወለጋ ዞን፣ በሰዮ ወረዳ በ2005 ዓ.ም. በመምህርነት ተቀጠረች።

ለትምህርት ከፍተኛ ፍቅር እንዳላት የምትናገረው አባይነሽ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ በሒሳብ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ2013 ዓ.ም. አግኝታለች።

ትምህርት በቃኝ ያላለችው አባይነሽ ከሁለት ዓመታት በኋላ በደምቢዳሎ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዋን ለመሥራት ጉዞዋን ጀመረች።

ከሁለት ዓመት በኋላ ትምህርቷን ስታጠናቀቅም የተመረቀችው በማዕረግ ሲሆን “የሜዳልያ ሽልማት ተቀብያለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የመጀመሪያዋ ዲግሪዋንም እንዲሁ ጥሩ ነጥብ በማግኘት የተመረቀች ሲሆን፣ የማስተርስ ዲግሪዋን ያጠናቀቀችው በ3.83 ውጤት ነው።

ያገኘችው ውጤት በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ‘የናቹራል ኤንድ ኮምፑቴሽናል ሳይንስ’ ዲፓርትመንት ከፍተኛ ከሆኑ ውጤቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

የአራት ልጆች እናት የሆነችው አባይነሽ የእናትነት ኃላፊነት፣ የማስተማር ሥራዋን፣ ጉሊት እና ትምህርቷን ጎን ለጎን ሳታዛንፍ ማካሄድ ያለበት ሲሆን “በምማርበት ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውኛል” ትላለለች።

ከምትጠቅሳቸውም ፈተናዎች ውስጥ “በ2016 መንታ ልጆቼን ወልጄ፣ አራስ ሆኜ ፈተና ተፈትኛለሁ” ስትል መንታ ልጆችን ወልዳ እንኳን ከትምህርቷ ወደ ኋላ እንዳላላች ትናገራለች።

የዶክትሬት ትምህርቷን ለመቀጠል ዕቅድ ያላት አባይነሽ፣ ህጻናት ልጆችን መንከባከብ እንዲሁም የገንዘብ ችግር እንዳለበት ታስረዳለች።