ዘወትር የሚባርቁት የአብይ አህመድ ጥይቶች ( አርበኛ ፋኖ አስረስ ማረ ዳምጤ )

ዘወትር የሚባርቁት የአብይ አህመድ ጥይቶች
““““““““““““““““““““““““`
አብይ “አነጣጥሮ” የሚተኩሰው ጥይት ሁሉ የሚባረቅበት ሰው ነው። ጥቂት ማሳያወችን እንመልከት:-
በአግባቡ ወንበሩን ሳያደላድል በጀመረው “የቀንጅብ ፖለቲካው” ከትግራይ የፖለቲካ ኃይል ጋር በገባው እሰጥ አገባ ምክንያት ብዙ እልቂት ያስከተለውን የሰሜኑን ጦርነት አዋለደ።
ለግዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ብሎ ኦሮምያ ክልልን ለኦነግ እንደሚሰጥ አስመራ ላይ የገባው ስዉር ስምምነት ዛሬ በአብይ እና በOLA መካከል በወለጋ፣ በሸዋ እና በቦረና አካባቢወች ቀጣይነት ያለው ጦርነት እንዲካሄድ ምክንያት ሆነ።
ከህወሃት ጋር ያደረገዉን ጦርነት ለመቋጨት ከአማራ ህዝብ ጀርባ የቆመረው የፕሪቶሪያውን ውል ለመተግበር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ። ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት 2015 ላይ የጀመረው አማራን ትጥቅ የማስፈታት እቅድ ዓለም በቂ ትኩረት ያልሰጠውን ግዙፍ ጦርነትን ይዞ መጣ። በዚህም ማርኮ የሚታጠቅ፣ መከላከያዉን የሚያንበረክክ የተደራጀ የአማራ ኃይል ተፈጠረ።
በራሱ የውስጥ ጦርነት ኤርትራንን የሙጥኝ ካለ በኋላ ፕሮጀክቱን ጨርሻለሁ ብሎ ሲያስብ ሻዕቢያን በመግፋት ይልቁንም የውስጥ ጉዳዩን አጀንዳ ለማስቀዬር ብሎ የቀይ ባህር ጌታ እሆናለሁ ማለት ሲጀምር በቀጠናው ላይ ይፈጠራል ተብሎ ያልተገመተን አዲስ ፀረ-አብይ የኃይል አሰላለፍ ወለደ።
ሱዳን ውስጥ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን በመደገፍ እና በአሶሳ ኤርፖርት በኩል ሎጅስቲክስ በማቅረብ አልቡራሃንን በማስገደድ ከኤርትራ እና ከትግራይ ኃይሎች እነጥላለሁ ብሎ የገባበት ጨዋታ የፖርት ሱዳንን መንግስት ፀረ-አብይ አሰላለፍ አፀናው።
ሱማሊያ ላይ እቀብጣለሁ ብሎ ሶማሊ ላንድን እውቅና ለመስጠት በአደባባይ የገባው ስምምነት ግብፅን ከነ ጦሯ ወደ ሶማሊያ ጎትቶ አመጣ። ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት አንካራ ሂዶ ሶማሊያን ይቅር በይኝ ብሎ ስምምነት ቢያደርግም እሱም ፉርሽ ሆኖበት ከየትኛውም ወገን ሳይሆን ቀረ።
የአዲስ ወደብ እና የባህር በር ፈላጊ ሆኖ ሲተውን ኢኮኖሚዋ በወደብ ክራይ ላይ የተመሰረተችዋን እና ከሁሉም ጎረቤቶች የተሻለ ትስስር የነበራትን ጅቡቲን አስኮርፎ ለግብፆች ተጨማሪ አጋር በመፍጠር ሌላ ክሽፈትን ወለደ።
የትግራይን ፖለቲካ መቆጣጠር ሲሳነው አፋር ውስጥ ፀረ-ህወሃት ታጣቂ ሲያደራጅ የትግራይን የውስጥ አንድነት መልሶ በመፍጠሩ ሌላ የፓወር አሰላለፍ ፈጥሮ ስልጣኑን የከፋ ስጋት ውስጥ ወደቀ።
ግድቡን ልንጨርሰው ነው መርቁልን ሲል በፓርላማው በተናገረው አሽሙር ውጤቱ ባይታወቅም ግብፅን እና ትራምፕን የተለዬ እልህ ውስጥ አስገባ።
አሁን ደግሞ IMF የእናት መቀነት ነው ብሎ በማቃለል የIMFን ፕሮጀክት ለመፈፀም የሚያስችል ሰላም እና የተረጋጋ እንቅስቃሴ በሌለበት በገባበት ወጥመድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ የኑሮ ጉስቁልና በመፍጠር ከጦርነቶች የተረፈው ህዝብ በነቂስ ይነሳበት ዘንድ በቂ ምክንያትን አሟልቷል ።
በአጠቃላይ አብይ ስሜት እንጅ ስሌት የማይገዛው፤ የፖለቲካ ድንክ ሆኖ ሳለ ብልሁ ምኒልክ ወንበር ላይ የተቀመጠ፣ ቀይ ባህርን በዲፕሎማሲ ብቻ የተቆጣጠሩት የእነ አክሊሉ ሐብተ ወልድ ወንበር ላይ ተራ ተላላኪወችን አስቀምጦ ሀገር የሚያዋርድ ሰው ነው።
አሳዛኙ ነገር አብይን መሪ አድርጎ የሚገዛለት ሰፊ ህዝብ እስካለ ድረስ የባረቁት የአብይ ጥይቶች ሰፊውን “ተገዥ” ህዝብ ለስቃይ፣ ለሞት እና ለስደት መዳረጋቸው ነው።
ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ በአረመኔው አገዛዝ ላይ የሚደረግን ሁሉንተናዊ ተጋድሎ በልዩ ትጋት እናስቀጥለዋለን። ከዳሞት እስከ መንዝ-ሞላሌ፣ ከደምበጫ እስከ መተማ፣ ከቡሬ እስከ እብናት፣ ከማቻክል እስከ ቦረና ሳይንት፣ ከራያ እስከ ክምር ድንጋይ የተፈፀመውም ይኸው ነው። ( አርበኛ ፋኖ አስረስ ማረ ዳምጤ )