ፌደራል መንግሥቱ ከሕወሓት ጋር ወደ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲገባ እንታገላለን

ሰሞኑን በመቀሌ የተዘጋጀው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ፣ ፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ከሕወሓት ጋር ወደ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲገባ ለመታገል መወሰኑን ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የሕወሓት ክንፍ ኦ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በጦርነቱ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ጉዳት በሽግግር ፍትሕ ስም የመሸፋፈን አካሄድ ሰፍኗል ያለው ኮንፈረንሱ፣ የሕግ ተጠያቂነት እንዲሠፍን ለመታገል እንደወሰነም ተገልጧል።

የታጠቁ ኃይሎች ከትግራይ ሙሉ በሙሉ ሳይወጡ፣ የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን አካሄድ እንዲቆም በጽናት ለመታገል ኮንፈረንሱ ከመግባባት ላይ መድረሱንም መግለጫው ጠቅሷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካሪ ምክር ቤት በማቋቋም ሽፋን ሥልጣን ለመጠቅለል ያደርገዋል ያለውን ሙከራ እንደማይቀበልና ይልቁንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሥልጣኑ እንዲወርድ ኮንፈረንሱ የጋራ ውሳኔ ላይ እንደደረሰም መግለጫው አመልክቷል።