ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር ከሥልጣን ለማንሳት ምቹ መደላድል ተፈጥሯል

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ሕወሓት፣ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር ከሥልጣን ለማንሳት ምቹ መደላድል ተፈጥሯል ማለቱን ሪፖርተር ዘግቧል።

የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ፈትለወርቅ ገብረ እግዚያብሄር፣ ቡድኑ የክልሉ ጸጥታ አመራሮች በጊዜያዊ አስተዳደሩ ዙሪያ መግለጫ ከማውጣታቸው በፊት ከአመራሮቹ ጋር ለቀናት የዘለቀ ውይይት ማድርጉን ትናንት ባንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ጌታቸው የሚመሩት ቡድን በትግራይ ላይ ከፍተኛ ክህደት እየፈጸመ ነው በማለት በድጋሚ የከሰሱት ፈትለወርቅ፣ ጌታቸው ከሥልጣን ሊያነሳቸው የሚችለው ፌደራል መንግሥቱ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው በማለት ወቅሰዋል ተብሏል።

ፈትለወርቅ ቡድናቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የያዙ አመራሮችን በራሱ ሹሞች የመተካት እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ ዓላማ እንደሌለው መግለጣቸውንም ጋዜጣው ጠቅሷል።