የትራምፕ ትዕዛዝ በጋምቤላ ክልል የሚሰጠው የተመጣጠነ የምግብ ድጋፍ እንዲቋረጥ አደረገ

የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች እንዲቋረጡ ማዘዙን ተከትሎ፣ ዓለማቀፉ የረድኤት ድርጅት አክሽን አጌነስት ሃንገር በጋምቤላ ክልል በስደተኞች መጠለያዎች ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠውን የተመጣጠነ የምግብ ድጋፍ ማቋረጡን ሮይተርስ ዘግቧል።

ድርጅቱ ፕሮግራሞቹን እንዲያቆም ዓርብ’ለት ትዕዛዝ እንደደረሰውና ትዕዛዙን ተከትሎ፣ በሳምንቱ መጨረሻ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ሕጻናትና እናቶች የተመጣጠነ ምግብ የሚያቀርብባቸውን ማዕከላቱን ለመዝጋት ዝግጅት እያደረገ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል።

ረድኤት ድርጅቱ እስካለፈው ታኅሳስ በነበረው የፈረንጆች ዓመት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ለየተጎዱ በጋምቤላ በስደተኛ መጠለያዎች ለ3 ሺሕ ሕጻናት የተመጣጠነ የምግብ ድጋፍ አድርጎ እንደነበር. የዜና ምንጩ አውስቷል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ዕርዳታ ለ90 ቀናት የማቆም ትዕዛዝ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍን እንደማይጨምር የተገለጠ ቢኾንም፣ የትኞቹ አሜሪካ የምትሠጣቸው ድጋፎች በአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ሥር እንደሚካተቱ ግን እስካኹን ግልጽ አልተደረገም።