በኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ተደራጅተው የጦር መሳሪያ እንዲገዙ ግዳጅ ተጣለባቸው

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች አንድ ለአምስት ተደራጅተው የጦር መሳሪያ እንዲገዙና የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ የመንግሥት መዋቅሮች ጫና እያደረጉ መኾኑ ታውቋል።

በተለይ አርሶ አደሮች በቡድን ለሚገዙት የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ፣ በአንድ አባውራ እስከ 10 ሺሕ ብር እንዲያዋጡ እየተገደዱ መኾኑን ምንጮች ተናግረዋል።

መዋጮውን የማይከፍሉ ነዋሪዎች በእስራት እንደሚቀጡ የገለጡት ምንጮች፣ መዋጮውን የሚሰበስቡት የቀበሌ መዋቅሮች ናቸው ብለዋል።

ኾኖም ለመሳሪያው መግዣ ገንዘብ የሚያዋጡ ነዋሪዎች፣ ሕጋዊ ደረሰኝ እየተሠጣቸው እንዳልኾነ ለማወቅ ተችሏል።

የግዴታ መዋጮው በተለይ በምዕራብ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።