የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በየቦታው የሚፈፀሙ ግድያዎች ተባብሰው መቀጠላቸውን ጠቆመ። ኢሰመኮ በዚህ የሩብ ዓመት ሪፖርቱ ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. አጋማሽ ያለውን ጊዜ የዳሰሱ ግድያዎችን እና አስገድዶ ስወራዎችን ዳስሷል። በቀጥታ እንዲህ ይቀርባል:
- በአማራ ክልል ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ፣ ቀበሌ 18፣ አዲስ ዓለም፣ ገንፎ ቁጭ፣ ቆሸ ሰፈር፣ ፋሲል ካምፓስ፣ አማኑኤል፣ ሎዛ ማርያም፣ አጣጥ እና አዘዞ በተባሉ የከተማው አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረው የትጥቅ ግጭት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተጸፈመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት እንዲሁም በሁለቱም ወገን በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሕፃናትን እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 10 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉና በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች እና የዐይን እማኞች ለማወቅ ተችሏል። ከአንድ ሆስፒታል በተገኘ መረጃ ብቻ በግጭቱ ምክንያት 6 ሴቶች እና 6 ሕፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 32 ሲቪል ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 1 ሰው ሆስፒታሉ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
- ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ከነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋር በተያያዘ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ዒላማን ባልለየ የጦር መሣሪያ ምክንያት ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 3 ሕፃናትን ጨምሮ በ5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ድርሷል። በተጨማሪ ቢያንስ 6 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።
- መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከዓለም በር ወደ ወረታ ሲጓዙ ወጅ የተባለ ቦታ ላይ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ጋር የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገድ ላይ አግኝተው እንዲሁም ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥተው የያዟቸውን በአጠቃላይ 10 ሲቪል ሰዎች ገድለው እንደሄዱ የዐይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ስናን ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ አቶ ጌታ እንዳለ አንማው እና አቶ አትንኩት ሁነኛው የተባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ከመኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ የገደሏቸው ሲሆን በሌሎች 4 መምህራን ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። በመምህራኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና ድብደባ በ2017 ዓ.ም. ትምህርት ለማስጀመር ካደረጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የመረጃ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።
- ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ቢቡኝ ወረዳ፣ ወይንውሃ ቀበሌ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ “ፋኖን ትደግፋላችሁ” እና “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” ያሏቸውን 11 ሲቪል ሰዎች በመያዝ ወይንውሃ ቀበሌ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ በመውሰድ እንደገደሏቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ፣ ውሻ ጥርስ በተባለ ጎጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በ8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል።
- መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ጉና በጌምድር ወረዳ፣ ክምር ድንጋይ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ አቶ ገደፋው አለሜ በተባሉ ሰው መኖሪያ ቤት ግቢ ላይ በማረፉ 2 የቤተሰቡ አባላት (ወ/ሮ ፍቅረዓለም አለበልና ሕፃን ዮርዳኖስ ገደፋው) ሲገደሉ ሌሎች 2 ሕፃናት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል።
- በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ በደባይ ጥላትግን ወረዳ፣ በቁይ ከተማ እና በዙሪያ ቀበሌዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረ ውጊያ በሲቪል ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በተለይ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት መጽሔት ልንገረው የተባለች የ3 ዓመት ሕፃን በተባራሪ ጥይት ተመትታ ቁይ ጤና ጣቢያ የሕክምና እርዳታ ከተደረገላት በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና “ሪፈር” ብትባልም መንገድ በመዘጋቱ እና በወቅቱ ሕክምና ባለማግኘቷ ሕይወቷ ማለፉን ከቤተሰቦቿ ማረጋገጥ ተችሏል። መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በውጊያው የሞቱ ሰዎችን ሥርዓተ ቀብር ሲፈጽሙ የነበሩ 3 ሲቪል ሰዎች “ለምን ትቀብራላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን፣ አንዱ መስማት የተሳነው አካል ጉዳተኛ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በቋራ ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ይካሆ እና ገለጉ (አሶል) ቀበሌዎች በመግባት ነዋሪዎችን “የብልጽግናን መንግሥት ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ከመከላከያ ጋር ሆናችሁ ፋኖን ተዋግታችኋል” በሚል 8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል። በተጨማሪም 60 የሚሆኑ ሰዎችን ገለጉ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት እንዳሰሩ እንዲሁም በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን እንደዘረፉ ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። ጥቃቱን በመፍራት በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን ከቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል።
- መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ዳጊ ቀበሌ ላይ በመንግሥት ኃይሎች በተደጋጋሚ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አቶ ሞገስ ደፈርሻ የተባሉ የ70 ዓመት አረጋዊ እንደተገደሉና 2 ሴቶች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ዳጊ ጤና ጣቢያ ላይ ጉዳት እንደደረሰ እና 4 መኖሪያ ቤቶች ተመተው እንደፈራረሱ ኢሰመኮ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በዕለቱ የአየር ጥቃት በተፈጸመባቸው ቦታዎችም ሆነ በቅርብ ርቀት ላይ ግጭት እንዳልነበረ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በቦታው እንዳልነበሩ ጨምረው ገልጸዋል።መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል ከተደረገ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የደጋ ዳሞት ወረዳን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ወደ ወረዳው መቀመጫ ፈረስ ቤት ከተማ በመግባት በርካታ የወረዳ አመራሮችን፣ ሥራ ኃላፊዎችን እና “የመንግሥት የመረጃ ምንጭ ናቸው” ያሏቸውን ቢያንስ 80 ሰዎች አስረዋል። እንዲሁም የወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ 3 መኖሪያ ቤቶችን በእሳት እንዳቃጠሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ከመስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት ሰዎች መካከል 38 ሰዎች ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ልዩ ቦታው ፈረስ ቤት ሚካኤል 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) እንደተገደሉ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስረድተዋል። ሁሉም ሟቾች ሲቪል ሰዎች (የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች) ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 22ቱ ሰዎች ኢሰመኮ በስም የለያቸው ናቸው።
- ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ፣ ገርጨጭ (መሃል ገነት) ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ አባላት አቶ ገብሬ ሙሉዬ እና አቶ መሀሪው መኩሪያ የተባሉ 2 ሰዎችን “ከፋኖ ጋር በመሆን ስትዋጉን ቆይታችሁ ነው ወደ ቤታችሁ የገባችሁት” በማለት ከቤታቸው አውጥተው እንደገደሏቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
- ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡20 አካባቢ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በደጋ ዳሞት ወረዳ፣ ፈረስ ቤት ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አማን እንየው የተባለ 1 የ4 ዓመት ሕፃን ልጅ ሲገደል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈረስ ቤት ቅርንጫፍ የሚገኝበት ሕንጻ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። የድሮን ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ፈረስ ቤት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደነበረ እንዲሁም በጥቃቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3፡20 ሰዓት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዝ ማማ ባሽ ንኡስ ወረዳ፣ “ጦስኝ አፋፍ” በተባለ አካባቢ በሚገኝ አንድ የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት ሲጠቀምበት የነበረ ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር (ድሮን) ጥቃት 2 ሕፃናትና 1 ሴት የተገደሉ ሲሆን በ5 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን እማኞች ገልጸዋል። ተጎጂዎቹ ከ5 ዓመታት በፊት በመሬት መንሸራተት ምክንያት ባሽ ቀበሌ “ወራና ጨታ” ከተባለ ጎጥ ተፈናቅለው በዚሁ ካምፕ ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። የድሮን ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት አካባቢው በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ሥር የሚገኝ እንደነበርና ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹ የመጠጥ ውሃ ለመቅዳት፣ ለመታጠብ እና ምግብ ለማብሰል ወደ ካምፑ ይመጡ እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።
- ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ ዞን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከወልድያ ከተማ ወደ ቃሊም ከተማ በተከታታይ የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ በሰው ሕይወትና አካል እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች እና የቤት እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ኢሰመኮ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። በወቅቱ ቃሊም ከተማ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር ብትሆንም የጦር መሣሪያ በሚተኮስበት ወቅት በአካባቢው ምንም ዐይነት የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበረ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. አቶ ተግባሩ ሽፌ አበበ የተባሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ የእህታቸውን ባል ተዝካር (የ“ፋኖ” አባል የነበረ) ታድመው ከደባይ ጥላትግን ወረዳ ሲመለሱ፣ በቁይ ከተማ አሰንዳቦ ፍተሻ ኬላ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። ግድያው የተፈጸመባቸው ሲፈተሹ የሟችን ፎቶግራፍ ይዘው በመገኘታቸው “ለምን ፎቶውን ይዘህ ተገኘህ?” በሚል እንደሆነና እስከ ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. እኩለ ቀን ድረስ አስከሬናቸው እንዳይነሳ ከልክለው እንዳቆዩት የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ለምባ አርባይቱ ቀበሌ፣ አርባ ተንሳይ ጎጥ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመግባት በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኝ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ ከሰበሰቡ በኋላ አቶ ነጋ ያለው (75 ዓመት)፣ አቶ አጉማሴ አዱኛ (45 ዓመት) እና አቶ ታእት ታከለ (34 ዓመት) የተባሉ 3 ሰዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት እንደገደሏቸው የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች አስረድተዋል።
- ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ብልባላ ከተማ በተፈጸመ የድሮን/የአየር ጥቃት እማሆይ ደስታ ካክራው የተባሉ የ83 ዓመት አረጋዊት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገድለዋል። በዚሁ ግቢ ውስጥ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ 2 የብልባላ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ጥቃት ከመድረሱ በፊት እና ከደረሰ በኋላ በአካባቢው የድሮን ድምጽ ይሰማ እንደነበር ለማወቅ ችሏል።
- ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ እናርጅ እናውጋ ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የተከሰተውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ቡሽት ኮኛ ቀበሌ፣ ግራርጌ ሰፈር በመጫወት ላይ ከነበሩ ሕፃናት መካከል ባንችግዜ አዲስ በተባለች የ5 ዓመት ሕፃን ላይ ሞት እና እባብሰው ጌቴ በተባለ የ6 ዓመት ሕፃን ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በተመሳሳይ ቀን በዚሁ ቀበሌ በሌላ መንደር በተፈጸመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት ወይዘሮ መደሰት ሞኜ የተባሉ የ42 ዓመት ሴት የሞቱ ሲሆን 1 ወጣት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኝ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
- ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ፋግታ ለኮማ ወረዳ፣ ፋግታ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር የነበሩ 12 የመንግሥት የጸጥታ አባላት እና ለጸጥታ አባላቱ ምግብ አቅራቢ የነበሩ 2 ሴቶች (ወይዘሮ ፈንታነሽ መላኩ እና ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም) በድምሩ 14 ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም 9 በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኙ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አባላት፣ 1 ሕፃን (ከላይ በስም የተጠቀሱት የሟች ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም የ2 ዓመት ሴት ልጅ) እና በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሻይና ቡና በመሸጥ የምትተዳደር 1 ሴት በአጠቃላይ 11 ሰዎች በጥቃቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የዐይን እማኞች አስረድተዋል።ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ገነተ-ማርያም ቀበሌ አርክን በተባለ ልዩ ጎጥ ሲያመርቱ የዋሉትን የጤፍ ምርት ለመጠበቅ አውድማ ተኝተው የነበሩ 5 የአንድ ቤተዘመድ አባላት የሆኑ አርሶ አደሮች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቀደም ብለው ከአካባቢው በመሸሻቸው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሲገቡ አውድማው ላይ ተኝተው ያገኟቸውን በግጭት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸውን አርሶ አደሮች እንደገደሏቸው ጨምረው ገልጸዋል።
- ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ደብረ ኤልያስ ወረዳ በጭነት መኪና ተሳፍረው በመጓዝ ላይ የነበሩ የደብረ ኤልያስ ወረዳ የመንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት 2 ሴት ሠራተኞች ጎዛመን ወረዳ ውግር ቀበሌ ሲደርሱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከመኪና አስወርደው ከወሰዷቸው በኋላ በማግሥቱ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ተገድለው እንደተገኙ የሟች ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሸካ ዞን አጎራባች ቀበሌዎች መካከል አልፎ አልፎ በወሰን አለመግባባት ምክንያት ግጭቶች የሚከሰቱ ሲሆን፣ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በዘለቀ ግጭት በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን፣ መንገሺ ወረዳ፣ የሪ ቀበሌ ጂፎር ንኡስ ቀበሌ ውስጥ 5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። እንዲሁም የተወሰኑ ነዋሪዎች የቤት ውስጥ ዕቃዎችን እና የእርሻ ሥራ መሣሪያዎችን ጨምሮ ንብረት ተዘርፏል።
- በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጃ ወለል ወረዳ፣ የላሎ ገለታ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ዳግም ኢገዙ እና አቶ ጸጋ ተክሌ የተባሉ 2 ሰዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ጋር “ግንኙነት አላችሁ፤ ስንቅ እና መረጃ ታቀብላላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ በዚያው ዕለት ማለትም መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።
- መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ ኢተያ ገምባ ጀቴ፣ ኢላላ እና ጢሮ ኢላላ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች “በአካባቢው ላለው የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል አቶ አለኸኝ አባተ፣ አቶ ተመቸው አርቄ፣ አቶ በለጠ ከበደ፣ አቶ ተመስጌን ተፈራ እና አቶ አስፋ ርቀው የተባሉ 5 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፡፡
- መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ኢተያ ገምባ ጀቴ ቀበሌ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አቶ ሙሳ ኑሩ፣ አቶ ኢብራሒም መሐመድ፣ አቶ ኢብራሒም ኡመር እና አቶ ጉልማ (ከ5 ቤተሰቦቹ ጋር) በአጠቃላይ 9 ሰዎችን ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል ገድለዋል።
- ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቤጊ ወረዳ፣ የኮበሬ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ መሐመድ ሀጂ ጀማል የተባሉ ሰው ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ አድርገሃል” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ በዕለቱ በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።
- ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ የወንዲ ዶች ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ምናለ ቃስም የተባሉ ሰው “ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።
- ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ ብርቢሣ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት “የመንግሥት አካላትን ተባብራችኋል” በሚል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ 17 ወንዶች እና 21 ሴቶች በአጠቃላይ 38 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። 78 መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል።
- ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ መጃ ላሉ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት በቀበሌው በሚኖሩ የጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ በምሽት ቤታቸውን በላያቸው ላይ በማቃጠል እና ጥይት በመተኮስ በአጠቃላይ 12 ሰዎችን ገድለዋል።
- ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በመቂ ከተማ 02 ቀበሌ ማንነታቸው በውል ባልታወቀ ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት መሆናቸው በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰቦች የተጠረጠሩ የታጠቁ አካላት በፈጸሙት ጥቃት 3 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አንድ የ12 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 4 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል።
- ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በአርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌሳ ረከታ እና መከና ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከሌሎች ነዋሪዎች ለይተው በፈጸሙት ጥቃት 13 ሰዎችን ከመኖሪያ ቤቶቻቸው በማስወጣት በጥይት ገድለዋል።
- ምንጭ ኢሰመኮ