በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃትና እንግልት እየደረሰ ነው

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ፣ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በሠላማዊ ዜጎች ላይ “ጥቃት” እና “እንግልት” እየደረሰ ነው ሲል መንግሥትን ወቅሷል።

ጸጥታ ኃይሎች በበዓሉ ማግስት፣ በአዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ቡሬና ደምበጫ “ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ፣ የአካል ጥቃት፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አስገድዶ መሠወር እና የንብረት ውድመት አድርሰዋል” በማለት ማኅበሩ ከሷል።

በተለይ ወጣቶች ከሚታሠሩባቸው ምክንያቶች መካከል፣ በዘፈን ታዋቂ የፋኖ መሪዎችን “አወድሳችኋል” የሚል እንደሚገኝበት ማኅበሩ ገልጧል።

ማኅበሩ፣ በተለይ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ “ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግፎችና እና ስደቶች” እንዲኹም “የዕምነት ነጻነትን የማፈን ተግባሮች” ያሳስቡኛል ብሏል።