ከአማራ ፋኖ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫና የአንድነት ጥሪ!

የእውነተኛ ወንድማማችነት ዋጋ ከአልማዝ ወይም ከወርቅ የበለጠ ውድ ነው!

ከአማራ ፋኖ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተሰጠ መግለጫና የአንድነት ጥሪ!

የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር በመመስረቱ የተሰማነን ታላቅ ደስታ ለመግለጽ እንወዳለን፣ እንኳን ደስ አላችሁም እንላለን። አንድነት ባለበት ሁሌም ድል አለ። ምክኒያቱም አንድ ስንሆን ጠንካራ፣ ስንከፋፈል ደግሞ ደካማ ስለምንሆን ነው። ለብቻችን ታግለን የተወሰኑ ድሎችን ልናገኝ እንችል ይሆናል፣ አብረን ከታገልን ግን ሙሉ ድል እናመጣለን፣ የአማራ ህዝብን ከጭቆና ቀንበር ነፃ እናወጣለን።

በመካከላችን ልዩነት አይኖርም ማለት አይደልም። ሁሌም የስልት እና ፍላጎት ልዩነቶች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። የድል አድራጊነት ዋናው መገለጫ በልዩነት ውስጥ አንድነት ፈጥሮ መታገል መቻል ነው። የትግል ስልታችንን አጣጥመን፣ ግለሰባዊ ፍላጎቶችን ገትተን አንድነት ማምጣት እና ትግላችንን በጋራ ማካሄድ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ እኛ በአማራ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ የመቀልበስ ግብን ያነገብን የህዝብ ልጆች ነን። ከዚህ ከትልቁ ግባችን አንፃር ሲታይ ያሉን ልዩነቶች ከዚህ ግባ የሚባሉ
አይደሉም።

በአንድ ላይ የቆሙ ትንሾች የተከፋፈሉ ብዙዎችን እንደሚያሸንፉ ሁሉ፣ ኃይላችን ያለው ከቁጥራችን መብዛት ሳይሆን በአንድነታችን ላይ ነው። የአማራ ህዝብ በቁጥር ብዙ ሆኖ እያለ እስካሁን ደካማ የሆነው አንድነት ባለመኖሩ ነው። በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ አንድነት የጎደለበትና የተሰባበረበት ምክኒያት ደግሞ የትግሉ ማዕከል የሆንነው እኛ አንድ መሆን ስላልቻልን ነው። በአንድ ስም ፋኖ ተብለን እየተጠራን፣ ለአንድ ዓላማ የአማራ ህዝብን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እየታገልን አንድ መሆን ግን አልቻልነም። ይባሱን ከራሳችን ጋር ጉልበት ወደ መለካካት እና የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እየገባን ነው።

ጥያቄው ምርጫችን ላይ ነው። እንደ ወንድማማችነት አብሮ ታግሎ፣ አብሮ ማሸነፍ እና አብሮ መኖር ወይም
አሁን እንደምናደርገው እንደ ሞኝ ተነጣጥሎ እና ተጠላልፎ መጥፋትን የአማራ ፋኖ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ምርጫው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እሱም እንደ ወንድማማችነት አብሮ ታግሎ፣ አብሮ ማሸነፍ እና አብሮ መኖር ነው። ይህን የእኛን ሀሳብ ሌሎች ወንድሞቻችንም ሀሳባቸው እንዲያደርጉት ጥሪ እያቀረብን
ከአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር ጋር የአንድነት ውይይት እንዲጀመር ጥያቄ እናቀርባለን። በአባቶቻችን መንገድ
ለአንድነት ተገዥ መሆን ያስፈልጋል። አንድነት ወደ ፊት ተጉዞ መሀል ላይ ለመገናኘት መወሰንን ይጠይቃል። የአማራ ፋኖ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ለእውነተኛ አንድነት ቅድመ ሁኔታ የለለው መሆኑን ለማሳውቅ እንወዳለን።

የጋራ ትግል፣ ለጋር ድል፣
ድል ለፋኖ፣ ድል ለአማራ ህዝብ፣
ራስ አርበኛ ደረጀ በላይ
የአማራ ፋኖ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ዋና አዛዥ