ቤንሻንጉል ጉሙዝ : የተገደሉት ሰዎች ብዛት 17 ነው; ከሟቾች መካከል 12 ህፃናት ናቸው

“ የተገደሉት ሰዎች ብዛት 17 ነው። ከሟቾች መካከል 12 ህፃናት ናቸው ” – የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል

በካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለ ጥቃት ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የክልሉ ምክር ቤት አባል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ፣ “የሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመዋል” ብለው፤ ከ10 በላይ ንጹሐን እንደተገደሉ፣ አብዛኛዎቹ ሟቾች ህፃናት እንደሆኑ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለ ጥቃቱ የጠየቃቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት አባልና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ኔኖ፣ “ ትክክል ነው። ንጹሐን ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ነው የተፈጸመው ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አባል በሰጡን ቃል በዝርዝር ምን አሉ ?

“ በካማሽ ዞን ምዥጋ ወረዳ አንገር ሜጢ የሚባል ታዳጊ ማዘጋጃ ቀበሌ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ/ም ንጋት 12 ሰዓት ጅምሮ የሸኔ ቡድን ጥቃት ፈጽሟል።

በዚሁ ጥቃት 16 ሰዎች እዛው ነው የሞቱት። አንደኛው ሰው ደግሞ ለህክምና ከሄደ በኋላ ነው የሞተው። የተገደሉት ሰዎች ብዛት 17 ነው። ከሟቾች መካከል 12 ህፃናት ናቸው። ቀሪዎቹ አዋቂ ናቸው።

ቡድኑ በተለያዩ ጊዚያቶች ጥቃት ሰንዝሯል። እስካሁን በተፈጸሙ ሦስት ጥቃቶች 27 ሰዎች ናቸው የተገደሉት።

የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ለኦሮሚያ ክልል አንድ ቀበሌ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ነው የሚገኘው። ጥቃቱ በወረዳው ከሚያዚያ ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመ ነው ” ብለዋል።

ምክንያቱና መፍትሄው ምንድን ነው ?

የታጣቂዎቹ ፍላጎታቸው ምንድን ነው ? መፍትሄውስ ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ “ ከምዥጋ ወረዳ የሸኔ ፍላጎት፥ አንደኛ አንገር ሜጢ በጣም ለምና ምርታማ ከሆኑ ቀበሌዎች መካከል ነው። ለም መሬት ስለሆነ አላማው ያንን ለመውሰድ ነው ” ሲሉ መልሰዋል።

“ ሁለተኛ ማህበረሰቡ ተረጋተቶ የእርሻ ሥራ እንዳይሰራ፣ ኑሮውን እንዳያሻሽል የአሻጥር ፓለቲካ አለ ” ብለው፣ “ መፍትሄው፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማህበሰቡን ማረጋጋት አለበት ”ነው ያሉት።

“ በሁለት ኪሎ ሜትር ግራና ቀኝ መከላከያዎች አሉ። መከላከያ በቅርብ ርቀት ባለበት በመካከል ገብተው ጥቃት ሲፈጽሙ በጊዜው ችግሩ ሳይሰፋ መድረስ ይችሉ ነበረ። ቀጣይም ችግሩ እንዳይሰፋ ቦታው ላይ የመከላከያ ኃይል በቋሚነት መቀመጥ አለበት ” ብለዋል።

አንድ የፓርላማ አባል በበኩላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፤ የትላንቱ ጥቃት መፈጸሙን እንደሰሙ ገልጸው፣ “ ከሦስት ሳምንታት በፊት በ8  ንጹሑን ሰዎች ላይ ጥቃት ደርሶ የሞቱበት ሁኔታ አለ ” ሲሉ አስታውሰዋል።