” በደብረብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ላልተፈለገ እርግዝና እና በአባላዘር በሽታ እየተጠቁ ነው ” የተፈናቃይ ሴት ወጣት ተወካዮች
⚫ ” የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ድርጅቶች አሁን ላይ ሁሉም ወጥተዋል ” የቻይና ካምፕ ተፈናቃይ አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ
በደብረብርሃን መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚሰጠው የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጥራቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ተፈናቃዮች መቸገራቸውን የተፈናቃዮቾ ሴት ወጣት ተወካዮች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በህክምና ባለሙያዎች ዘንድም ሚስጥር ጠባቂ አለመሆን አገልግሎት ለማግኘት በምንሄድበት ወቅት የማሸማቀቂያ ቃላቶችን የሚጠቀሙ በመሆኑ አገልግሎቱን ማግኘት ከብዶናል ብለዋል።
“የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት እየሰጠ ያለው ዩኒሴፍ ብቻ ነው፣ አገልግሎት የሚሰጠውም ግቢ ውስጥ ቢሆንም ሴት ልጅ ስትገባ የእንትና ልጅ የወሊድ መቆጣጠሪያ ልትጠቀም ገበች ይላሉ፣ ስንወጣ ደግሞ ወጣት ወንዶች ይጠብቁና ያሸማቅቁናል” ሲሉ ችግራቸውን ይገልጻሉ።
በተጨማሪም ” የህክምና ባለሙያው ወንድ ነው፣ ይህ ደግሞ ሴቶች በነፃነት የሚፈልጉት እንዳይናገሩ አድርጓል፣ በከተማው ጤና ጣቢያዎች ስንሄድም በነፃ ስለሆነ የሚሰጠው ምን ልታደርጊ ትመጫለሽ ውጪ ይላሉ። እነሱ የሚፈልጉት ብር የሚከፍለውን ሰው ብቻ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ወጣት ሴቶችም በየፋርማሲው መድሀኒት እየገዙ ይውጣሉ፣ አብዛኞቹም ለህመም እየተዳረጉ ነው ብለዋል።
በስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት እጥረት በርካታ ወጣቶች ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለአባላዘር እና ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች መጋለጣቸውንም አስረድተዋል።
“በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉ ወጣት ወንዶች ተስፋ እየቆረጡ አልኮል እየጠጡ ሴት ልጆችንን አስገድደው እየደፈሩን ነው፣ ስንጠይቅም በቸልተኝነት ሁሉም ይስተካከላል ይላሉ” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርቧል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የቻይና ካምፕ የተፈናቃይ ኮሚቴ አስተባባሪ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ እሸቱ ውበቱን አነጋግሯል።
ምክትል ሰብሳቢው ምን አሉ ?
“በደብረብርሃን መጠለያ ካምፖች ውስጥ የጤና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ድርጅቶች ወጥተዋል። አሁን ምንም አይነት የጤና አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም።
እየተደፈርን ነው ያሉት ባለኝ መረጃ ውሸት ነው፣ ነገር ግን አንድ ወጣት ለመድፈር ሲሞክር ተይዞ ማረሚያ ቤት ነው ያለው።
እያተሸማቀቁን ነው ያሉት እውነት ሊሆን ይችላል፣ ለእኛ ግን እስካሁን የደረሰን መረጃ የለም፣ በህክምና እጥት ግን ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ተጨማሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሀሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። በዚህ ጉዳይ መረጃ ለመስጠት ፈልጋለሁ የሚል ማንኛውንም አካል የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።