በርካታ የጤና ባለሙያዎች ከሥራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ መታሰራቸው ቀጥሏል

ኢሰመኮ፣ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ከሥራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ እየታሠሩ፣ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸውና ከማስተማሪያ ሆስፒታሎች በግዳጅ እንዲወጡ እየተደረጉ መኾኑን ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኢሰመኮ፣ በአዲስ አበባ፣ ጂማ፣ ባሕርዳር፣ ሀዋሳ እና ጎንደር በርካታ ሬዚደንትና ተለማማጅ ሐኪሞችን ጨምሮ በርካታ የጤና ባለሙያዎች እንደታሠሩና በግዳጅ ከማስተማሪያና የሥራ ቦታቸው ከኾኑ ሆስፒታሎች እንዲወጡ እንደተደረጉ ገልጧል። ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚወሰዱ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች የሰብዓዊ መብቶች መርኾዎችን የተከተሉ መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል። ችግሩን ለመፍታት ውይይት እንዲደረግና ተጠያቂነት እንዲሠፍን የጠየቀው ኢሰመኮ፣ አፈና አዋጭ መንገድ አይደለም ብሏል።