በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ተማሪዎች አንድነት፣ የዘንድሮው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ በሚስተዋሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አላተኮረም በማለት ተችቷል። ማኅበሩ፣ በትግራይ የሚገኙ አሕጉረ ስብከቶች ከሲኖዶሱ ከተለዩ በኋላ በተስተዋሉ ጥፋቶች ዙሪያ ያዘጋጀውን ሰነድ ለቋሚ ሲኖዶስና ለፓትርያርኩ ማቅረቦ ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሷል። መምሪያው፣ በኦሮሚያ ክልል በአስተዳደራዊ ችግሮች ቤተክርስቲያናት እየተዘጉ፣ ካህናትና ተከታይ ምዕመናንም እየፈለሱ መሆኑን ገልጧል። የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነትና የአሕጉረ ስብከት ጽሕፈት ቤቶች የአስተዳደር ዘርፍ ከሊቃነ ጳጳሳት ውጪ በብቁ ባለሙያዎች እንዲመሩ የጠየቀው መምሪያው፣ የቤተክርስቲያኗ ተቋማት ለምዝበራ ተጋልጠዋል ብሏል።