” መንግስታት ውጤት አልባ ከሆነ የIMF የበጀት መቀነስና ዕዳ መክፈል ፖሊሲ ወጥተው ትኩረታቸውን ዜጎቻቸው ላይ ማድረግ አለባቸው ” – አክሽን ኤድ

” መንግስታት ውጤት አልባ ከሆነ የIMF የበጀት መቀነስና ዕዳ መክፈል ፖሊሲ ወጥተው ትኩረታቸውን ዜጎቻቸው ላይ ማድረግ አለባቸው ” – አክሽን ኤድ

በአፍሪካ ስድስት ሃገራት በጤና እና ትምህርት ዘርፉ በጀት በመቀነሱ ሰራተኞች የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አዲስ ጥናት (https://actionaid.org/sites/default/files/publications/The%20Human%20Cost%20of%20Public%20Cuts%20May%202025.pdf) አመላከተ።

ጥናቱን አክሽን ኤድ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት የሰራው ሲሆን ፦
– በኢትዮጵያ
– በጋና
– በኬንያ
– በላይቤሪያ
– በማላዊ
– በናይጄሪያ 600 የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ነው ተብሏል።

በጥናቱ ከተሳተፉት መሃል 97 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች የሚያገኙት ደመወዝ መሰረታዊ የሚባለውን ወጪያቸውን ለመሸፈን እንደማያስችላቸው ተናግረዋል።

97 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች በደመወዛቸው የቤት ኪራይ መክፈል፣ የምግብ እና ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን እንዳልቻሉ አንስተዋል።

በጥናቱ በ6ቱ ሀገራት የሚገኙ የጤና ተቋማት ተገልጋዮች በሃኪሞች እጥረት እና በዋጋ መጨመር ደስተኛ አይደሉም ሲል ያስቀመጠ ሲሆን መንግስታት ውጤት አልባ ከሆነ የIMF የበጀት መቀነስና ዕዳ መክፈል ፖሊሲ ወጥተው ትኩረታቸውን ዜጎቻቸው ላይ ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ህመምተኞች ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ ረጅም መንገዶችን እንደሚጓዙ፤ የወባ መድኃኒትም በ10 እጥፍ ዋጋው መጨመሩ በጥናቱ የተካተተ ነው።

ለአብነትም በኢትዮጵያ ሙያከላ ቀበሌ የምትኖር ሴትን በመጥቀስ ከ5 አመት በፊት የወባ መድሃኒት በ50 ብር ትገዛ እንደነበር እና አሁን ግን ከግል ተቋማት በ500 ብር እንደሚገዛ መናገሯን ገልጿል።

በሌላ በኩል ፥ በጥናቱ ከተሳተፉት 87 በመቶ የሚሆኑት መምህራን የክፍል ውስጥ ቁሳቁሶች /የማስተማሪያ ቁሳቁሶች እንዳልተሟሉላቸው ሲገልፁ ፤ 73 በመቶ ያህሉ የትምህርት ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ከኪሳቸው አውጥተው እንደሚገዙ ተናግረዋል።

84 በመቶ መምህራን ደመወዛቸው ባለፉት 5 አመታት ከ10 እስከ 50 በመቶ በሚሆን መጠን የቀነሰ መሆኑ ተመላክቷል።

ለዚህ ሁሉ ቀውስ አክሽን ኤድ መንግስታት በትምህርት እና ጤና ላይ የሚያወጡት ወጪ መቀነሱ ነው ሲል ያስቀመጠ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምም (IMF) መንግስታት የመከረበት መንገድ መኮነን አለበት ሲል ገልጿል።

አይ ኤም ኤፍ መንግስታት እንደ ትምህርት እና ጤና ባሉ ልማቶች ላይ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ይመክራል ያለው አጥኚው ተቋም፥ በማሳያነት በናይጄሪያ በ2024 ከሃገራዊ ገቢዋ 4 በመቶ ያህሉን ለጤና ስታውል 20 በመቶ ያህሉን ዕዳ ለመክፈል አውላለች ነው ያለው።

በተለምዶ አንድ ሃገር የበጀቷን አንድ አምስተኛ ለትምህርት ማዋል አለባት ቢባልም በጥናቱ ከተካተቱት ስድስት ሃገራት ውስጥ አራቱ የትምህርት በጀታቸው ከዚህ መጠን በታች ነው።

አክሽን ኤድ መንግስታት እና IMF እየሄዱ ያሉበትን መንገድ በመቀየር ለነዚህ ዘርፎች ትኩረት በመስጠት የሰራተኞቹን ኑሮ እንዲያሻሽሉ እና ዜጎችም ጥራት ያለው ትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

የአክሽን ኤድ ጥናት ስለ ጤና ባለሙያዎች ምን ይላል ?

አክሽን ኤድ በአፍሪካ ስድስት ሃገራት በጤና እና ትምህርት ዘርፉ ላይ አካሂዶ ይፋ ባደረገው ጥናት 32 በመቶ (የሀገራቱ አማካኝ) የሚሆኑት የጤና ባለሞያዎች በክፍያ ማነስ ምክንያት ሞያውን ለመልቀቅ በማሰብ ላይ ይገኛሉ ሲል ገልጿል።

ጥናቱን ፦
🇪🇹በኢትዮጵያ
🇬🇭በጋና
🇰🇪በኬንያ
🇱🇷በላይቤሪያ
🇲🇼በማላዊ
🇳🇬በናይጄሪያ 600 የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ነው ያካሄደው።

በጥናቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ምላሽ በሪፖርቱ የሰፈረ ሲሆን የቀረቡት ጥያቄዎችም እ.አ.አ 2020 ጋር በማነጻጸር የቀረቡ ስለመሆናቸው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያውያኑ የጤና ባለሞያዎች ምላሽ ምን ይመስላል ?

– ስልሳ አምስት በመቶ (65%) የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች በክፍያ ማነስ ምክንያት ሞያውን ለመልቀቅ በማሰብ ላይ ይገኛሉ። (በጥናቱ ከተሳተፉ 6 ሀገራት ትልቁ ነው)

– መቶ በመቶ (100%) የሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች የጤና መገልገያ ቁሶችና መድኃኒት እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል። (በጥናቱ ከተሳተፉ 6 ሀገራት ትልቁ ነው)

– ሰባ አምስት በመቶ (75%) የሚሆኑት ለቤተሰቦቻቸው የሚያቀርቡት የምግብ መጠን መቀነሱን አንስተዋል።

– መቶ በመቶ (100%) የሚከፈላቸው ክፍያ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

– ዘጠና በመቶ (90%) የሚሆኑት የበጀት ቅነሳ እናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ብለው ያስባሉ።

– ዘጠና አምስት በመቶ (95%) የሚሆኑት ለጤናው ዘርፍ በቂ በጀት አልተመደበም ብለው ያምናሉ።

– ሀምሳ ሶስት በመቶ (53%) የሚሆኑት የታካሚዎች ቁጥር ጨምሯል ብለው ያምናሉ።

– መቶ በመቶ (100%) የሥልጠና ዕድሎች ቀንሰዋል ብለው ያምናሉ።

– ሰባ አምስት በመቶ (75%) የሚሆኑት ሞያቸው የግል ህይወታቸው ላይ (Work-life Balance) ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል።

– መቶ በመቶ (100%) የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው እየሰፋ መምጣቱን አንስተዋል።

ጥናቱ መንግስታት ውጤት አልባ ከሆነ የIMF የበጀት መቀነስና ዕዳ መክፈል ፖሊሲ ወጥተው ትኩረታቸውን ዜጎቻቸው ላይ ማድረግ አለባቸው ሲል ምክረ-ኃሳብ ያስቀምጣል።

በአቡጃ ስምምነት መሰረት የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት ከአጠቃላይ በጀታቸው 15 በመቶ የሚሆነውን ለጤናው ዘርፍ እንዲያውሉ ይጠበቃል።