ልክ የዛሬ አመት በዚህ ወር በምርመራ ክፍል ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደለው ኢሳያስ በላይ የተሰራ የምርመራ ዘገባ!
ለስድስት አመታት ያህል በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ውስጥ ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል።
በ2014 ዓ/ም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልሉ ሰላምና ደኅንነት የሚጠቀምበት ወታደራዊ ሬዲዮ የመለያ ኮዱ በቀላሉ ተጋላጭ ሆኖ ተገኘ። ይህንን የሬዲዮ ትስስር እንደ አዲስ ማስተሳሰር ግድም ሆነ።
ኢሳያስ በላይ የወታደራዊ ሬዲዮ ትስስሮች እንዲሁ በቀላሉ የሚከወኑ አይደለም። በዘርፉ ልምድ ያላቸው አለም አቀፍ ተቋማት ተወዳድረው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚጠይቁበት ስራ ነው።
አገርን ለከፍተኛ ወጪ የዳረገ የሬዲዮ ግንኙነት መረብ እንዲሁ በቀላሉ የይለፍ ቃሉ ተሰብሮ ሚስጥሮች የሚባክኑ ከሆነ ደግሞ ሌላ የአገራዊ ደኅንነት ስጋት ነው።
ይህ ስጋት በ2014 ዓ/ም በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላም እና ደኅንነት የሬዲዮ መገናኛ ላይ በግልፅ ታየ።
ችግሩ እንዴት ይቀረፍ? በሚል ኢንሳ መፍትሄ ሲያፈላልግ ኢሳያስ በላይ በተቋሙ ውስጥ ያገኘውን አለም አቀፍ ልምድ በመውሰድ የክልሉን የሬዲዮ አውታር እንደ አዲስ ለማቀናጀት ሀሳቡን አቀረበ።
ኢንሳ ሰባት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን አዋቅሮ ኢሳያስን የቡድኑ መሪ አድርጎ ወደ አማራ ክልል ሸኘው።
ቡድኑን በማስተባበር የአማራ ክልልን ከወረዳ ጀምሮ እስከ ዋናው ቢሮ ድረስ ያለውን የሬዲዮ ትስስር በዘመናዊ መልኩ አቀናጅቶ ለክልሉ መንግስት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አስረክቧል።
ኢሳያስ ዛሬ በሕይወት ባይኖርም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ደኅንነት ቢሮ እስከ ወረዳ ድረስ የሚጠቀሙበት የሬዲዮ መገናኛ መረብ በዚህ ድንቅ ወጣት የተሳሰረ ነው።
ኢሳያስ በላይ ለምን ተገደለ?
የአማራ ክልልን የሬዲዮ መገናኛ አውታር አቀናጅቶ ከተመለሰ ከሁለት ወር በኋላ አንድ ቀን ጧት 4:00 ሰዓት ላይ ቢሮ ከመግባቱ የኢንሳ የውስጥ ደኅንነት እና ጥበቃ ኃላፊ የኢሳያስን መታወቂያ ቀማው።
በኢንሳ ተቋም ውስጥ የውስጥ ደኅንነት እና የጥበቃ አባል የሰራተኞችን መታወቂያ ቀምቶ ከወሰደ ቢሮ መግባት የተከለከለ ነው።
ኢሳያስም ለምን መታወቂያው እንደተወሰደበት ቢሮ ገብቶ ኃላፊውን መጠየቅ አልቻለም። ከስራ እንዳሰናበቱት ቆጥሮ ሌላ ስራ ማፈላለግ ያዘ።
ከወራት በኋላ አማራ ባንክ ተቀጥሮ ለሁለት አመታት ያህል በሙያው እየሰራ ባለበት ወቅት ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ/ም ከምሽቱ 2:30 የፌደራል ፖሊሶች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ትፈለጋለህ በሚል ይዘውት ወጡ።
በማግስቱ ባለቤቱ እና የቅርብ ቤተሰቦቹ አዲስ አበባን ሲያካልሉ ውለው ማታ አዲስ አበባ ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አገኙት። በምን ጠርጥረው እንዳሰሩትም እርሱም አላወቀም።
ከሁለት ቀን በኋላ ከ14 ተጠርጣሪዎች ጋር ወደ አፋር ክልል ሰመራ ጉዞ ተጀመረ። ሰመራ ከተማ መግቢያው አካባቢ አንድ የግለሰብ ግቢ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው በዕለቱ ከምሽቱ 4:00 ሰዓት እስረኞቹ በየተራ እየተጠሩ በመርማሪዎች ይጠየቃሉ።
“የኢሳያስ ተራ ደረሰ” ይላል ከኢሳያስ ጋር አብሮ የነበረ ስሙን እንዳይገለፅ የጠየቀን አንድ ወጣት።
እኔ ይላል ይሄው ወጣት “አራት መርማሪዎች በየተራ እየተነሱ እውነቱን ተናገር እያሉ በጥፊ እና በእርግጫ እየደበደቡ አድክመውኛል፣ በዛ ላይ እጅግ ይሞቃል። መቆም አቅቶኝ ተዝለፍልፌ ወድቂያለሁ። እጅ እና እግሬን ይዘው በሩ ላይ ጣሉኝ። ኢሳያስን ይዘውት ሲመጡ ይታየኛል። ሊቢያ ውስጥ በአሸባሪዎች እንደ ታረዱት ወጣቶች ጀርባውን ጨምድደው ወደ ታች ደፍቀው ይዘውት ገቡ። እጁን ወደ ኋላ አዙረው በካቴና አስረውታል። ወደ ግርግዳው ፊትህን አዙር ሲሉት ይሰማኛል” በማለት የሚያስታውሰውን ምልልስ እንዲህ ያስረዳል።
“ማነው ስምህ?”
“ኢሳያስ በላይ”
“የት ነው የተወለድከው?”
“ጎንደር”
“ለምን እንደ ታሰርክ ታውቃለህ?”
“አላውቅም”
“ምን አባህ ሆነህ ነው የማታውቀው?”
ሌሎቹ እየደበደቡት አንዱ ይጠይቃል: “ለምንድን ነው የማታውቀው?”
“አላውቅም! ከቤቴ ነው ይዘውኝ የመጡት”
“ከፋኖዎች ጋር ምን ነበር ስታወራ የነበረው?”
“ከማንም ጋር አውርቼ አላውቅም?”
“ስልካችሁ እንዳይጠለፍ ምን አድርጉ ነው ስትላቸው የነበረው?”
አሁንም የእርግጫ እና የጥፊ ድምፅ ይሰማኛል።
“ይናገራል ቆይ” ሲል አንዱ ገልጋይ ሆኖ ተከሰተ።
“በሕይወት መኖር ከፈለግህ ተናገር ካልሆነ አስከሬንህን እዚህ ነው በእሳት የምናቃጥለው”
የእሱ ድምፅ አይሰማኝም
“ልጆች አሉህ አይደል?”
“ተናገር እንጂ!”
እንዲናገር ተንጫጩበት፣ የእሱ ድምፅ አሁንም አይሰማም።
አንዱ በምን እንደ መታው ባላውቅም ኢሳያስ “አአአአአአአአ ….. ብሎ ሲወድቅ ተሰማኝ። ከወደቀበት በእግራቸው ሲደበድቡት አንደኛው “አሁን ይናገራል ተውት” ብሎ አስቆማቸው።
ኢሳያስ መሬት ላይ እንደ ተኛ ያቃስት ነበር።
“ለፋኖ ስልካችሁ እንዳይጠለፍ ምን አድርጉ ብለህ እንደ ተናገርህ ካላወጣህ አስከሬንህን ለጅብ ነው የምንሰጠው፣ ልጆችህን ድጋሜ አታያቸውም”
ሁለቱ መርማሪዎች የክፍሉን ሙቀት መቋቋም ያቃታቸው ይመስላል። ሲወጡ እኔ መኖሬንም ረስተው “ይሄን ነው በደንብ ጠይቁት ያለው ኮማንደር” ሲል ሰማሁት።
“ማን ነበር ስሙ?” አንደኛው ጠየቀ
“ኢሳያስ” አለው ሌላኛው
አንደኛው መርማሪ የእስረኞቹን ክፍል ከፍቶ ሁለት እስረኞችን ይዞ መጣና “ይዛችሁት ግቡ” ብሎ አንጠልጥለው ክፍሌ ውስጥ አስገቡኝ።
ኢሳያስ በላይ ምርመራ ክፍል ውስጥ አድሮ ጧት እንደ ጨርቅ ሰውነቱ ልሞ በእስረኞች ተደግፎ መጣ። ሙቀቱ እሳት ነው። የሚሰጠን ውሃ በቀን ግማሽ ሊትር ከአንድ ዳቦ ጋር ነው። ሁላችንም ተዳከምን።
ወደ መጨረሻው ቀን ኢሳያስን እና እኔን በመኪና ራቅ ያለ ቦታ ይዘውን ሄዱ። እልም ያለ በረሀ ነው። ከመኪና አስወርደው ሁለት እጅ እና እግራችንን በካቴና አስረው “እዚህ በረሀ ላይ ጅብ ነው የሚበላችሁ። ማንም አይደርስላችሁም። እውነቱን ብትነግሩን ይሻላል” ሲል አንዱ መርማሪ ጠየቀን።
እኔ ከማንም ጋር ተገናኝቼ እንደማላውቅ ነገርኩት። ኢሳያስ ደካክሞ ስለነበር የሚለው አይሰማም። እኔን መልሰው መኪናው ላይ አንስተው ጫኑኝ። ኢሳያስን ትተነው ሄድን።
የተወሰነ ርቀት ከተጓዝን በኋላ እኔንም አውርደው ጥለውኝ ሄዱ። ሁለት እግሮቼ እና ሁለት እጆቼ በካቴና የታሰሩ በመሆናቸው በፍፁም መንቀሳቀስ አልችልም።
ለመገላበጥ አያመችም እንጂ ከምርመራ ግቢው የተሻለ አየር አገኘሁ። ነፃነትም ተሰማኝ። ነገር ግን አውሬ ቢተናኮለኝ መከላከል እንደማልችል ሳስብ ደግሞ ስጋት ገባኝ።
በግምት ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን የመኪና ድምፅ ቀሰቀሰኝ። አንድ በማስክ እስከ አፍንጫው ድረስ የተሸፈነ መርማሪ ጋቢና ውስጥ ብቅ ብሎ በተኛሁበት ቁልቁል እየተመለከተ፣
“ጅብ አልበላህም?” ሲል አብሮት ያለው ሹፌር ሳቀ።
ሁለት ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ፖሊሶች አንስተው ማታ ከጣለችን ሽፍን ወታደራዊ ተሽከርካሪ ውስጥ ጣሉኝ። ትንሽ ከተጓዝን በኋላ ኢሳያስን አገኘነው።
“ይሄም ሰውዬ አለ። የዚህ አገር ጅብ ምን ነካው? በአፉ እንድናጎርሰው ፈልጎ ነው?” ሲል ሰማሁት
ለቃቅመው ወደ ምርመራ ካምፕ መለሱን።
ከቀኑ 10:00 ሰዓት ሲሆን መርማሪዎቹ ኢሳያስን ጠርተውታል። እስረኛው ስለተዳከመ እና አቅም ስላነሰው እንደ በፊቱ አንዱ አንዱን ደግፎ መሄድ አልቻለም። ራሳቸው ፖሊሶች ሰቅስቀው አንስተው ይወስዱናል። ኢሳያስንም እንደዚሁ አድርገው ወደ ምርመራ ክፍል አስገቡት።
ምርመራ ክፍል አስር ሰዓት ገብቶ 12:00 ላይ ይዘውት ወጡ። እሱ ከምርመራ ክፍል ሲወጣ እኛ ለሽንት ወጥተን ተገናኘን። ሆዱ አካባቢ ደም በደም ሆኗል።
ከላዩ ላይ ውሃ የተደፋበትም ይመስለኛል። ልብሱ ሁሉ በስብሷል። እስከ ሱሪው ድረስ በደም ተነክሯል። ደም እና ውሃ ከሰውነቱ ይወርዳል። ፖሊሶቹ በር ላይ ስለጣሉት ዝልፍልፍ ብሎ ተኛ። ጠጋ ብዬ ሳየው ሆዱ ተቀዶ የውስጥ ክፍሉ ይታያል።
ጠጋ ብዬ በእሱ በኩል አለፍኩ። መራመድ አቃተኝ። ኢሳያስ አልኩት። አልመለሰልኝም።
የሚደበድቡን በተቆረጠ የፌሮ ብረት ነው። ብረቱ ጫፉ ላይ ሲቆረጥ ትንሽ ሰየፍ ያለ በመሆኑ እሱ ሁላችንንም ብዙ ቦታ እየቆረጠን ደም ፈሶናል። ብዙ ደም ስለፈሰሰን ሰውነታችን ገርጥቷል። ኢሳያስንም ያገኘው ይሄው ብረት ነው። ብረቱ ጫፉ ላይ ስለት እንዳለው ስለሚያውቁ የሚመቱን በስለቱ በኩል ነው።
በኋላ መርመሪዎቹ ከምርመራ ክፍል ወጥተው ወደ ህክምና ልንወስደው ነው ገንዘብ አዋጡ አሉን። ከቤታችን ስንያዝ ኪሳችን ውስጥ የነበረችውን በሙሉ አሰባስበን ሰጠን። ይዘውት ወጡ። በማግስቱ እኛንም ወደ አዲስ አበባ ይዘውን ተመለሱ” ሲል የደረሰባቸውን ግፍ ለመሠረት ሚዲያ ተናግሯል።
መርማሪዎቹ የኢሳያስን አስከሬን ለቤተሰቦቹ ሲያስረክቡ “ለማንም ቢሆን ታስሮ እንደነበር እንዳትናገሩ” ብለው የዛሬ ዓመት ግንቦት 7 ቀን አስከሬኑን አስረከቧቸው።
ኢሳያስ በላይ የሁለት ልጆች አባትና ባለ ትዳር ነበር።
ዘገባው የመሠረት ሚዲያ ነው።